ሕዝብ የሚያለያይ ሳይኾን ሕዝብን የሚያገናኝ ትርክትን ማስቀጠል እንደሚገባ የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች አሳሰቡ።

35

ጎንደር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የአማራ ክልል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተከብሯል። በበዓሉም የተለያዩ የክልል መሪዎች ተገኝተዋል። የአፋር ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አሲያ ከሚል የአማራ ክልል ምክር ቤት ባደረገው ጥሪ መሠረት የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል ለማክበር በታሪካዊቷ መናገሻ ጎንደር ከተማ መገኘታቸውን ገልጸው ለተደረገላቸው አቀባበልም በአፋር ሕዝብ ስም አመሥግነዋል።

ክልላዊ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር አብሮነት እና እኩልነትን ያሳየ መኾኑን አንስተው የብሔረሰብ ቀን አብሮነትን ያጠናከረ፣ ልዩነቶችን ያጠበበ እና የሚያስተሳስር ቀን ነው ብለዋል። የቀደመ ፍቅርን በመመለስ ሰላምን አጠናክሮ የሀገርን ልዕልና ከፍ ለማድረግ ሁሉም ለሀገር ሰላም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የሚያለያዩ ትርክቶችን በመተው አንድ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመገንባት እና ሕዝብን የሚያለያይ ሳይኾን የሚያገናኝ ትርክትን ማስቀጠል እንደሚገባም አንስተዋል። ችግሮችን በራስ አቅም በውይይት መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል። የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ሲከበር የሕዝብ ትስስር፣ አንድነት፣ ፍቅር እና ባሕል እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው ያሉት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ስዓዳ አብዱረህማን ናቸው።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የስኬት ጎዳና እንዲሳካ ለማድረግ ብሔር ብሔረሰቦች ትናንት በአንድነት ቆመው ለሀገር እንደታገሉ እና መስዋዕትነት እንደከፈሉ ሁሉ ዛሬም አብረው ቁመው ለሀገር አንድነት ሊተጉ ይገባል ብለዋል። ችግሮችን በውይይት በመፍታት እና በመቀራረብ የሕዝቡን ጉዳት ለማስቀረት እና የጋራ ሀገርን ለመገንባት የጸጥታ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሰላም እንዲጸና የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል። የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታየ ከበደ ጎንደር የታሪክ፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ ከተማ ናት ብለዋል። በከተማዋ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ መኾኑን አንስተዋል። ጎንደር የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ናት ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ የጎንደር ሕዝብ አቃፊ መኾኑን አይተናል ብለዋል።

በቀጣይ ሌሎች ወደ አካባቢው መጥተው የከተማዋን ቅርስ እንዲጎበኙ እና የጎንደርን ፍቅር እንዲመለከቱ ይሠራልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአምራች ወገኖችን ሕይወት የሚቀጥፈዉን ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ለመከላከል በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና አንዱ የገነባውን ሌላው ማፍረስን ሳይኾን ማስቀጠል እንደሚገባ የታየበት ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)