
ጎንደር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት እና የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት በተያዘላቸዉ ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረዉ ቀጥለዋል። የልማት እንቅስቃሴዉን አስመልክቶ ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከከተማ አሥተዳደሩ የተወጣጡ የሥራ ኀላፊዎች ምልከታ አድርገዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በከተማዋ የጎንደርን ገናና ታሪክ የሚመጥኑ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነዉ ብለዋል። አፈጉባኤው የኮሪደር ልማቱ እና የፋሲል አብያተ መንግሥታት የእድሳት ሥራዎች ደረጃቸዉን ጠብቀዉ እየተከናወኑ መኾኑን አንስተዋል። የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ የጎንደርን ታላቅነት መልሶ ያመጣ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኔስኮን መመዘኛ ጠብቆ በመሠራቱ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
በጎንደር እና አካባቢዉ በርካታ ፀጋዎች መኖራቸዉን ያስታወሱት አፈጉባኤው ሀብቶችን ተጠቅሞ ማልማት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በጎንደር አቅራቢያ የተገነባው የጎርጎራ ፕሮጀክት ለአካባቢው ትልቅ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
የሕዝቡን የረዥም ዓመታት ጥያቄ ለመፍታት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የጎንደርን ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ደግሞ የሰላም ግንባታ ላይ የተጀመሩ ተግባራትን አጥብቆ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነዉ ያነሱት። በክልሉ እና በአካባቢው እየታዩ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!