
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በልማት ሥራዎች ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እያደረገ ነው። በውይይቱ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በከተማዋ ውበትን የሚገልጡ እና ለትውልድ የሚተላለፉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ሃብት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ልማት በመንግሥት ብቻ የሚከወን አለመኾኑን ያብራሩት ምክትል ከንቲባው ልማትን ማኅበረሰቡ መደገፍ አለበት ነው ያሉት። ልማት በማኅበረሰብ ሲደገፍ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እንደሚያደርገውም አንስተዋል።
የከተማዋ ግብር ከፋዮች ለከተማዋ ልማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ከተሞችን ውብ አድርገው የሚፈጥሯቸው ነዋሪዎቿ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከተሞች የሕልም ውጤቶች ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባው የሀገር ሥልጣኔ መገለጫዎች እና የርእዮተ ዓለም መነሻ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ባሕር ዳርን ከዓለም ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። አባቶች በከተማዋ የሠሩትን በማድነቅ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ ይገባዋል ነው ያሉት። ተፈጥሮ የሰጣትን ዓባይ እና ጣናን በመጠቀም የተሻለች ከተማ መገንባት ይጠበቃልም ብለዋል።
ባሕር ዳር የትምህርት ከተማ የሚል ስያሜ የተሰጣት የቱሪዝም እና የውበት ከተማ መኾኗን ነው ያነሱት። ውቧን ከተማ የበለጠች ውብ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኮሪደር ልማቱ ትልቁ ዓላማ ሕዝብን ለመጭው ዘመን ማዘጋጀት እና መጭውን ዘመን ለሕዝብ ማዘጋጀት ነው ብለዋል።
ከተማዋን ጽዱ፣ ጤናማ እና ሳቢ ለማድረግ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ስማርት ሲቲን የመገንባት ሂደቶች ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ምቹ ያልኾኑ ነባር መንገዶችን ማስፋት፣ ያረጁ፣ የደከሙ ቤቶችን፣ የተረሱ ሠፈሮችን በማሻሻል ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ የኮሪደር ልማቱ ሌላኛው ዓላማ መኾኑን ነው የተናገሩት። በከተማዋ ደረጃ በደረጃ 22 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማት ሥራዎች ጥራት ዋናው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!