
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ለ4 ሚሊዮን ሕጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ መኾኑን ገልጿል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሕዳር 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ለስድስት ቀናት የሚቆይ የፖሊዮ መከላከል ክትባት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ክትባቱ በመስከረም ወር የተሰጠ ቢኾንም አሁንም ለተከሰተው ወረርሽኝ ምላሽ የሚሰጥ መኾኑን ጠቅሰዋል። ክትባቱ የሚሰጠው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ሲኾን በዚህም 4 ሚሊዮን ሕጻናትን ለመከተብ መታቀዱ ተገልጿል።
ከ25 ሺህ በላይ ክትባት የሚሠጡ እና ከ8 ሺህ በላይ አስተባባሪዎች በሚሳተፉበት የጸረ – ፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በቤት ለቤት፣ በሕጻናት ማቆያ፣ በትምህርት ቤቶች እና በተፈናቃይ ማቆያ ጣቢያዎች ይሰጣል ነው የተባለው።
ሕጻናት ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም በአሁኑ ዘመቻ ይከተባሉ ነው የተባለው። በዘመቻው ከፖሊዮ በተጨማሪ ሌሎች ክትባቶችም ስለሚሰጡ እና የአጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግር ያለባቸው ሕጻናት ልየታም ስለሚደረግ ወላጆች ዕድሉን እንዲጠቀሙበት አቶ በላይ አሳስበዋል።
በመግለጫው ፖሊዮ ሙሉ በሙሉ ከሀገር እስኪጠፋ ድረስ ተመሳሳይ ዘመቻ ስለሚደረግ ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲተባበር ተጠይቋል።
ፖሊዮ በክልሉ የተከሰተው በአንድ አካባቢ ብቻ ቢኾንም ፖሊዮን በሀገር እና በዓለም ደረጃ ለማጥፋት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ዘመቻ አካል መኾኑንም አክለዋል።
ፖሊዮ ለዘላቂ የአካል ጉዳት እና ሲከፋም ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። ስለኾነም የጸረ – ፖሊዮ ክትባት በመስጠት ሕጻናትን መታደግ እንደሚገባም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!