በህጻናት የሕይዎት መንገድ ላይ የተደቀነው ጦርነት።

39

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ያለው የጸጥታ ችግር የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ያለ ቢኾም በተለይ በሕጻናት መብት እና ደኅንነት ላይ የደቀነው አደጋ ከባድ ነው። ሕጻናት እንደልብ መጫዋት፣ መቦረቅ ይፈልጋሉ፤ በትምህርት ቤታቸው ዕውቀትን ማግኘት ሲገባቸውም ከቀናት በፊት የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳወጣው መረጃ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ልጆች ከገበታው ዕውቀት እዳይቀስሙ ኾነዋል።

የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቋቋመው የክልሉ ሴቶች እና ሕጻናት ጉዳዮች ቢሮ በሕጻናት ላይ እየኾነ ያለውን ሁሉ ቢያውቅም ጥቃቱን ለማስቆም እጁ ዝሏል። በቢሮው የሕጻናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አሻግሬ ዘውዴ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በሕጻናት ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች እየደረሱባቸው መኾናቸውን ተናግረዋል።

ሕጻናት የሌሎችን እገዛ የሚፈልጉ በመኾናቸው ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ኾኗል የሚሉት ዳይሬክተሩ ለጎዳና ተዳዳሪነት፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ እና ለፆታዊ ጥቃት እየተዳረጉ ነው ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ በተጠፈጠረው ጸጥታ ችግር ብቻ ባይባልም 920 ሺህ ሕጻናት ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው።

በሁሉም ቦታዎች ተደራሽ ለመኾን የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት እንደኾነ የገለጹት ዳይሬክተሩ እንደቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ቀውስ የደረሰባቸው ሕጻናትን ለመደገፍ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። እንደ ክልሉ ሴቶች እና ሕጻናት ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ሕጻናት ከክልሉ ሕዝብ 50 ነጥብ 8 በመቶ ይሸፍናሉ። የክልሉን ሕዝብ ግማሽ ያህሉን የሚሸፍኑት ሕጻናት እነርሱ ባልፈጠሩት ችግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ኾነዋል።

በሕጻናት እንክብካቤ እና ማቆያ ላይ የሚሠራው የኦፕሪፍስ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ዳንኤል ግዛው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከቀያቸው ፈልሰው ወደ ባሕር ዳር ከተማ የሚመጡ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ማስተዋላቸውን ነግረውናል። ወደ እነርሱ ማዕከል የሚመጡ ሕጻናት ትምህርታቸውን ያቋረጡ፣ የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው በመኾናቸው ተስፋ የቆረጡ እና ግራ የተጋቡ መኾናቸውን ጠቅሰው ነው ሃሳባቸውን ያጋሩን።

ሕጻናት በማይፈልጉት ሕይዎት ውስጥ ገብተው እየኖሩ እንዳለ መረዳታቸውን የነገሩን አቶ ዳንኤል ብዙ ሕጻናት በቤት ሠራተኛነት ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል። አቶ ዳንኤል እንደሚሉት ከሁሉም በላይ ሕጻናቱ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው ነው እየረበሻቸው ያለው፤ የወደፊት ሕይዎታቸውም ብዙ ያሳስባቸዋል።

የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር እስጢፋኖስ እንዳላማው እንደሚሉት ደግሞ ጦርነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልጆች የሕይዎት መንገድ ላይ ደርሶ እየቆመ የወደፊት ርምጃቸውን እየገታው መጥቷል፡፡ ልጆች ጫናን የመቋቋም አቅማቸው እና ዝግጁነታቸው ዝቅተኛ በመኾኑ እንደዚህ አይነት ችግር ሲጋጥማቸው ሰማይ የተደፋባቸው ያህል ነው የሚሰማቸው ይላሉ፡፡

ይህም የአጭር እና የረጅም ጊዜ አዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግር ይፈጥራል ብለዋል። ልጆች ከትምህርት ገበታቸው መቅረት፣ መደፈር እና ለመሰል ችግሮች መጋለጥ ለአዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ዶክተር እስጢፋኖስ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ሕጻናት እየደረሰባቸው ካለው ከአዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንዲወጡ ከተፈለገ የሀገሪቱ የጤናው ዘርፍ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ማዕከል ያደረገ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ መሥራት ይገባዋል ብለዋል።

ሌላው እና ዋናው መፍትሄ ግን የጦርነት አዙሪቱን ማስቆም መቻል ነው ይላሉ ዶክተር እስጢፋኖስ። ጦርነቱን ማስቆም ካልተቻለ ምንም ያህል የአዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ሥራ ቢሠራ ከሥነ ልቦናዊ ቀውሱ መውጣት እንደማይቻል ዶክተር እስጢፋኖስ ያምናሉ።

በሕጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግርን ችላ እያልን ካለፍነው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጥር ያላቸውን ስጋት ለአሚኮ አጋርተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋና ዋና ከተሞች ዘመናዊ የግብይት ማዕከላትን በማስፋት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየሠራ እንደኾነ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበአማራ ክልል ለ4 ሚሊዮን ሕጻናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው።