
ደሴ: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ ለሚገነባው የአንደኛ ደረጃ የግብይት ማዕከል የግንባታ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ፣ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር )፣ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በደሴ ከተማ በሮቢት ቀበሌ የግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የግብይት ማዕከሉ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በከተማ አሥተዳደሩ እና በክልሉ መንግሥት ትብብር እንደሚገነባ ገልጸዋል። ማዕከሉ ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል ባለፈ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚያስችል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች በስፋት ይቀርቡበታል ብለዋል።
የግብይት ማዕከሉ ሲጠናቀቅ አምራች እና ሸማቹን በቀጥታ ከማገናኘት ባለፈ ጅምላ አከፋፋዮችም ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ያስችላል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር ) መንግሥት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በመለየት እየሠራ መኾኑን ገልጸው የማዕከሉ ግንባታም የዚህ አንድ አካል እንደኾነ ተናግረዋል።
የአንደኛ ደረጃ የግብይት ማዕከል ግንባታው በአራት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ያሉት ኀላፊው ለሥራው ውጤታማነት ኅብረተሰቡ ተባባሪ እንዲኾንም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግሥት በጀት በመመደብ በዋና ዋና ከተሞች ዘመናዊ የግብይት ማዕከላትን ለማስፋት እየሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሕገ ወጥነትን በመከላከል ያለአግባብ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ያስችላል ነው የተባለው።
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!