የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚካሄደው ሥራ ሁሉም እንዲሳተፍ ጤና ቢሮ አሳሰበ፡፡

54

ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኤች አይ ቪ በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ እየተሰራጨ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ጨምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች በኤች አይ ቪ ኤዲስ ክትትል እና ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተገልጿል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ወደ 41 የሚኾኑ የተፈናቃይ ጣቢያዎች አሉ። በእነዚህ ጣቢያዎች ውስጥ ወደ 87 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለቫይረሱ ከሌላው ማኅበረሰብ የበለጠ ተጋላጭ እንደኾኑ ነው የሚገለጸው፡፡ አሁን ባለው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያትም እየጨመሩ ያሉ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችም ለቫይረሱ ሥርጭት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑም ነው የተብራራው፡፡

በሩብ ዓመቱም ወደ 1 ሺህ 65 የሚጠጉ ልጃገረዶች አስገድዶ መደፈር እንደተፈጸመባቸው እና እነዚህም ለቫይረሱ ተጋላጭ የመኾን ዕድላቸው ከፍ ያለ ስለመኾኑ ነው የሚነገረው፡፡ እነዚህ ክስተቶች ለኤች አይ ቪ ስርጭት መስፋፋት ዓይነተኛ ምክንያቶች መኾናቸውንም በጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመ ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ግብዓቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ በየጊዜው የመንገድ መዘጋቱ ደግሞ የኤች አይ ቪ ታካሚዎች መድኃኒቶችን በቀጠሯቸው ወቅት በመውሰድ እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡ ቫይረሱ በፍጥነት እየተሰራጨ ካለባቸው አካባቢወዎች መካከል ደሴ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተማ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ አሁን ላይ የኤች አይ ቪ ስርጭት ሲታይ ከጠቅላላው የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ 61 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች መኾናቸውን አቶ ውድነህ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የኾኑ እና የከፋ የኤች አይ ቪ ስርጭት ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማዕከል በማድረግ የአቻ ለአቻ ውይይት የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡ ተጋላጭ የኾኑትን እንዲመረመሩ፣ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን ህክምና እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩ፡፡

በክልሉ 173 ሺህ 463 ኤች አይ ቪ በደማቸው ይኖርባቸዋል ተብለው በጥናት የተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከእነዚህ ውስጥ 157 ሺህ 972 ሰዎች ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ 156 ሺህ 91 የሚኾኑት ደግሞ ሕክምናቸውን ጀምረው እየተከታታሉ መኾናቸው ተገልጿል፡፡ በአዲስ ከሚያዙት ውስጥ 67 በመቶ የሚኾኑት ከ30 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ መኾናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የኤች አይ ቪ ኤዲስ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ በሚሠራው የመከላከል ሥራ ተሳትፎ በማድረግ እና ድጋፍ እና እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው በመደገፍ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራው በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል” ዣንጥራር ዓባይ
Next articleበዋና ዋና ከተሞች ዘመናዊ የግብይት ማዕከላትን በማስፋት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየሠራ እንደኾነ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።