“የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራው በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል” ዣንጥራር ዓባይ

80

ደሴ: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት አሥተባባሪ ጃንጥራር ዓባይ በደሴ ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት የሥራ ሁኔታን ጎብኝተዋል። የኮሪደር ልማት ተጠቃሚ ከኾኑት የአማራ ክልል ከተሞች አንዷ የኾነችው ደሴ ከተማ በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ ቧንቧ ውኃ እየተባለ ከሚጠራው ስፍራ እስከ ባሕል አምባ የሚዘልቅ የኮሪደር ልማት ሥራን ጀምራለች።

የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ያለበትን ሁኔታ የሚገመግም እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመስጠት ያለመ ጉብኝትም ተካሂዷል። የዕድገት ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አሥኪያጅ ከበደ መሐመድ የተሰጣቸውን ኀላፊነት ከታሰበው አንፃር በጥሩ ሁኔታ እየፈፀሙ እንደኾነ ተናግረዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ አጀማመሩ ላይ መዘግየት ቢኖርም በተጀመረ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጥሩ አፈፃፀም እንዳለው ገልጸዋል።

ደሴ ከዚህ በኋላ ተጀምሮ የሚያድር የልማት ሥራ እንዳይኖራት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ማኅበረሰቡም ይህን ተረድቶ የአካባቢውን ሰላም አስጠብቆ እንዲዘልቅ እና ባለሃብቱም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የደሴ ኮሪደር ልማት አስተባባሪ ጃንጥራር ዓባይ የኮሪደር ልማቱ የሥራ ሁኔታ ጥሩ አፈፃፀም ላይ የሚገኝ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

መሪዎችም ሥራውን በትኩረት እየሠሩ ያለ በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከጉብኝቱ በኋላ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ካለው ልምድ አንፃር የታዩ ክፍተቶች ካሉ አስተያየቶችን እንደሚሰጡም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በጉብኝቱ የደሴ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላም ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የክልሉ ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ተናገሩ፡፡
Next articleየኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚካሄደው ሥራ ሁሉም እንዲሳተፍ ጤና ቢሮ አሳሰበ፡፡