
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተጠሪ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አልካባሮቭ (ዶ.ር) እና በኢትዮጵያ ከሚሰሩ የተመድ ኤጀንሲዎች ጋር በባለብዙ ዘርፎች የትብብር መስክ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እንደ ተመድ መሥራችነቷ ድርጅቱ መርኾዎቹን ተከትሎ ተልዕኮ እንዲሳካ ቀጣይነት ባለው መንገድ በንቃት የምትንቀሳቀስ ሀገር መኾኗን ገልጸዋል። መንግሥት ባስቀመጣቸው ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ መስኮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የድርጅቱ ድጋፍ ከሀገሪቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር ተናብበው መከናወናቸው ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ኀብረተሰብ ክፍሎችን ሕይዎት በማሻሻል ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መኾኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል። ኢትዮጵያ በተመድ የተቀመጡ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት በድርጅቱ ጥላ ሥር የሚገኙ ኤጄንሲዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተጠሪ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዶ.ር) ራሚዝ አልካባሮቭ እና የተመድ ኤጄንሲዎች ተወካዮች በኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው መስኮች ዙሪያ ተባብሮ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!