“የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕዝቡን የጤና ስጋት በመለየት ምላሽ እየሠጠ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

67

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) እና ሌሎችም መሪዎች በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተገኝተው ሥራውን ተመልክተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ኢንስቲትዩቱ ለሕዝብ ጤና የሚሠራ ቁልፍ ተቋም ነው ብለዋል። የሕዝቡን የጤና ስጋት እየለየ ምላሽ እየሰጠ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተቋቁመው አርዓያነት ያለው ሥራ አከናውነዋል ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ።

በተለይም በዚህ ዓመት በክልሉ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ከፍተኛ የጤና አደጋ ሳያደርስ በመከላከል በኩል ኢንስቲትዩቱ የሕዝብ አደራውን እየተወጣ ነው ብለዋል። የገጠሙ ውስንነቶችን በጋራ በመፍታት ሕዝብ የሚጠብቀውን የጤና አገልግሎት ማሟላት እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይም በዚህ ዓመት በክልሉ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ከፍተኛ በመኾኑ እና የበሽታው ባህሪም የተለየ ስለነበር ኢንስቲትዩቱ ይህንን ችግር ለመፍታት የጥናት ሥራዎችን እያከናዎነ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የጤና መረጃ ማዕከል ኾኖ እያገለገለ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በዘርፉ ላይ ጥናት ለሚያደርጉ አካላትም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ኢንስቲትዩቱ በሰው ኀይል የተሟላ እንዲኾን የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ዶክተር ሙሉነሽ እንዳነሱት የኢንስቲትዩቱ ሕንጻ በውስጡ ከሚከናወኑ ሥራዎች ብዛት አኳያ ሲታይ ጠባብ መኾኑን አንስተዋል። ኢንስቲትዩቱን የሚመጥን ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችል መሬት በከተማ አሥተዳደሩ በኩል እንደተፈቀደለትም ጠቁመዋል። በጀቱ እንደተገኘም ግንባታው ይጀመራል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጤነኛ እና አምራች ትውልድ ለመፍጠር አጋዥ የኾነ ማዕከል ነው ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ ያሉበትን ችግሮች በመለየት መፍትሄ ለመስጠት እና ለላቀ አገልግሎት ለማዘጋጀት አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ክልሉ ከጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት ዘልቀው ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ የሚችሉ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ በመከላከል በኩልም ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለበት ዶክተር ዘሪሁን አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሌሎችም ክልሎች ልምድ ሊቀሰምበት የሚችል ተቋም ነው ብለዋል። በኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የጤና ምርመራ አቅሞች መፈጠራቸውንም አንስተዋል። ጠንካራ የጤና መረጃ ማዕከል ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመለየት እና ምላሽም ለመስጠት በአንድ ማዕከል ኾኖ ጠንካራ ሥራ እያከናወነ ሥለመኾኑም አንስተዋል። የፌዴራሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎችን እና የሚመለከታቸው አካላትን ሁሉ የኢንስቲትዩቱን ሥራዎች በመደገፍ የተሻለ የኅብረተሰብ ጤና መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየንግዱ ማኅበረሰብ ሕግን አክብሮ በመሥራት ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ አሳሰቡ።
Next articleተመድ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።