“ጤናማ ሀገርን ለመገንባት ጤናማ ትውልድን መፍጠር የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል” ጤና ሚኒስቴር

28

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእናቶችን፣ ህጻናትን፣ የአፍላ ወጣቶችን እና ወጣቶችን ጤና ለማሻሻል እየተሠሩ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዋነኛው ጉዳይ መኾኑን በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ማርያማዊት አሰፋ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የእርግዝና መከላከያ ሥርጭት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2000 ከነበረበት 6 በመቶ በ2019 ወደ 41 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። በቀጣይ 2030 ደግሞ ወደ 54 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚወልዱ100 ሺህ እናቶች ይሞቱ የነበረውን 1 ሺህ 30 እናቶች ወደ 267 እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል።

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አጠቃቀም ላይ ለውጥ ቢመጣም አሁንም ግን 22 በመቶ የሚኾኑ በትዳር ላይ የሚገኙ ሴቶች አገልግሎቱን እየፈለጉ በተለያዩ ምክንያቶች የማያገኙ መኖራቸውን ገልጸዋል። በዚህም ኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትኾን አድርጓታል። ለዚህ ደግሞ 45 በመቶ የሚኾነው የሕዝብ ቁጥር ከ15 ዓመት በታች የሚገኝ መኾኑ እና አንድ ሦስተኛው ሕዝብ ደግሞ ከ10 እስከ 24 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኝ መኾኑን በማሳያነት አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023 እስከ 2025 ባለው ጊዜ የእርግዝና መከላከያ ሥርጭት መጠን አሁን ካለበት 41 በመቶ ወደ 45 በመቶ ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ሀገሪቱ በ2030 የቤተሠብ እቅድ መርሐ ግብርን ለማሳካት የገባቸውን ሥምምነት ለማሳካት የቤተሠብ እቅድ አገልግሎት ጥራት ማሻሻል፣ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማስፈን፣ የግብዓት አቅርቦትን ቀጣይነት ማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። የቤተሰብ እቅድ ሕይወትን የሚታደግ በመኾኑ ሴቶች ምርጫቸውን ባከበረ መንገድ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እንደሚደረገም ነው የገለጹት።

ያልታቀደ እርግዝና እንዳይከሰት እና የሴቶችን ጤንነት ለመጠበቅ ወንዶችም የቤተሠብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲጠቀሙ እና ለሴቶች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።

ጤናማ ሀገርን ለመገንባት ጤናማ ትውልድ መፍጠር የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች የጎንደር ኮሪደር ልማትን ጎበኙ።
Next articleየንግዱ ማኅበረሰብ ሕግን አክብሮ በመሥራት ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ አሳሰቡ።