
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የፊታውራሪ ገበየሁ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደየዝንባሌያቸው እና ፍላጎታቸው የሙያ ትምህርቶችን ለመማር ጠይቀዋል፡፡ ተግባር ተኮር የሙያ ሥልጠናው ለቀጣይ ኑሮ ጥሩ መሠረት የሚጥል በመኾኑ ተግባራዊ እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉም ነው ያስገነዘቡት።
አስተያየታቸውን ያጋሩን ርእሳነ መምህራን የሙያ ትምህርቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የመማሪያ ክፍሎችን የማዘጋጀት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ የመምህራን እጥረት፣ የግብዓት ችግር እና ሥልጠናውን ለመስጠት የሚያግዙ መጽሐፍቶች በሶፍት ኮፒ ብቻ መዘጋጀታቸው በሚፈለገው ልክ ወደ ትግበራ ለመግባት እንዳይቻል አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ የሙያ ትምህርቶችን በ2017 የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ በግል የሙያ ትምህርቶችን ተምረው የትምህርት ማሻሻያ ያልተያዘላቸው መምህራን በሠለጠኑበት ሙያ እንዲያስተምሩ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
የሙያ ትምህርቱን ሙሉ በሙሉ በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ 31 ተጨማሪ መምህራን ያስፈልጋሉ ያሉት ኀላፊዋ ይህንን ለማሟላት የበጀት እጥረት ያጋጠመ በመኾኑ ባለው የሰው ኀይል ሥልጠናውን ለማስጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ከክልል የመጣው መጽሐፍ በሶፍት ኮፒ መኾኑን የገለጹት ወይዘሮ መቅደስ ታትመው እስኪመጡ ድረስ ኮፒ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ ጊዜያት መጽሐፍቱ ታትመው ለተማሪዎች ተደራሽ እንዲኾኑ ትምህርት መምሪያው ጥያቄውን ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ማቅረቡን አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!