የአገልግሎት አሰጣጥ አሠራሮችን እያዘመነ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።

39

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን የጸረ ሙስና ቀንን በውይይት አክብሯል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

በውይይቱ ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመታገል በታማኝነት፣ በቁርጠኝነት እና በቅንነት መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል። የአሠራር አለመዘመን ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንደሚያደርግም ተገልጿል። በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ በሥነ ምግባር የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥ የማዕዘን ድንጋይ ነው ተብሏል።

የመንግሥት አገልግሎቶች በታማኝነት፣ በፍትሐዊነት እና በተጠያቂነት እንዲመሩ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል። የሥነ ምግባር መርኾዎችን በማክበር በአገልግሎት ሰጪዎች እና በዜጎች መካከል መተማመን መፍጠር ይገባልም ተብሏል። የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን አማካሪ ኃይለልዑል ተስፋ የሕዝብ ተቋም በመኾኑ አሠራሩ የተስተካከለ መኾን ይገባል ብለዋል። የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል።

አሠራሮችን ለማዘመን የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን እየሠጡ መኾናቸውንም ገልፀዋል። ማኅበራትን ማዘመን ዋና ሥራ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ሰፊ መኾናቸውን የተናገሩት አማካሪው ከመሥሪያ እና ከመሸጪያ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ በወቅቱ ኦዲት ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች አሉ ነው ያሉት።

ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እቅዶችን አውጥተው እየተገበሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የአሠራር ሥርዓታቸውን ጠንካራ እንዲያደርጉ እና የአግልግሎት አሰጣጣቸው እንዲዘምን እየሠራን ነው ብለዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ የሚገኙ ተቋማት አቅማቸው ካደገ ችግሮች ይፈታሉ ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ደህንነት ጥበቃ ዳይሬክተር አንዱዓለም በላይ ብልሹ አሠራርን የመቆጣጠር እና አሠራሮችን የማዘመን ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልፀዋል።

የአሠራር ጥሰቶች ሲኖሩ የማስተካከል ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል። የሠራተኞችን የመፈጸም አቅም የማሳደግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች የተሻለ ለመፈጸም እንደሚያግዛቸውም ገልፀዋል። በተቋማት አሠራሮችን የማጠናከር እና አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀጣይ የሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleየነገ ሕልማቸውን ለማሳካት ተግባር ተኮር የሙያ ሥልጠና እንዲሠጣቸው በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች ጠየቁ፡፡