የጸረ ሙስና ቀን በዓልን ከማክበር ባለፈ በቁርጠኝነት ሙስናን መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ።

45

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን የጸረ ሙስና ቀንን በውይይት አክብሯል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የጸረ ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል።

በውይይቱ ጽሑፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ የዝና ደስታ ለውጤታማ አሥተዳደር እንቅፋት ከሚኾኑ ጉዳዮች መካከል ሙስና እና ብልሹ አሠራር ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል። የሕዝብ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከኢ-ፍትሐዊ አሠራር እና ከብልሹ አሠራር መውጣት ይገባል ነው ያሉት። አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከሙስና የጸዳ አገልግሎት መሥጠት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ሙስና እና ብልሹ አሠራር የመንግሥትን ታማኝነት እንደሚቀንስም ገልጸዋል። የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሠጣጥን የተሻለ በማድረግ ሙስናን መታገል እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ሙስና ለሰላም እጦት፣ ለሕግ መጣስ እና ለሌሎች ችግሮች እንደሚዳርግም አመላክተዋል። ሥራን በሕግ እና በሥርዓት ብቻ መከወን እንደሚገባም ተናግረዋል። የምጣኔ ሃብት ችግር ሲኖር ሰዎችን ወደ ሙስና ሊያስገባቸው አንደሚችል ነው የተናገሩት።

የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ተጠያቂነት ሲጠፋ እና በሌሎች ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ወደ ሙስና የሚገቡ እንደሚበረክቱ ነው የተናገሩት። ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ እንደሚያቀጭጭም ተናግረዋል። በሀገር ደኅንነት ላይም አደጋ እንደሚያሳድርም ገልጸዋል። ሙስና ሲሰፋ በሥነ ምግባር ብልሹ የኾነ ትውልድ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም አመላክተዋል።

ሙስናን ለመታገል መንግሥት አስተማማኝ፣ ተገልጋዮችን የሚያረካ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይገባዋል ብለዋል። ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የሕዝብ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል። የሕዝብ አመኔታን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ እና ልማታዊ ግቦችን ለማሳካት ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት መስጠት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ዜጎች የመንግሥት ተቋማት ታማኝ መኾናቸውን የሚገነዘቡት የሚያገኙት አገልግሎት ቀልጣፋ እና ግልጽ ሲኾን ነው ብለዋል። የመንግሥት የአገልግሎት አሠጣጥ የተሻለ ሲኾን የዜጎች እርካታ ያድጋል፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ አኩልነትን ያበረታታል፣ ተቋማዊ ቅልጥፍናን እና ተጠያቂነትን ያሻሽላል፣ የፖሊሲ ትግበራን ያጠናክራል፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ይደግፋል፣ የዜጎችን ተሳትፎ ያሳድጋል፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ውጥረቶችን ይቀንሳል ነው ያሉት።

ቀልጣፋ ያልኾኑ ሥርዓቶች እና ሂደቶች፣ ደካማ ዕቅድ፣ ወጥነት የጎደለው ክትትል፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር፣ ገንዘብን ያለ አግባብ መጠቀም፣ ወገንተኝነት እና አድሎአዊነት፣ የብቃት ማነስ እና ደካማ የሥራ ሥነ ምግባር፣ የቴክኖሎጂ እጦት እና ሌሎች ምክንያቶች የመንግሥት አገልግሎት ደካማ እንዲኾን ያደርጋሉ ብለዋል።

የመንግሥት አገልግሎት ደካማ ሲኾን የሕዝብ አመኔታ እንዲሸረሸር፣ ማኅበራዊ አለመመጣጠን እንዲኖር፣ የሙስና እና ብልሹ አሠራር ድርጊቶች እንዲጨምሩ፣ የሕዝብን ቁጣ እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲደክሙ ያደርጋል ነው ያሉት። የመንግሥት ሠራተኞች መልካም አገልግሎት በመስጠት ሙስናን መከላከል አንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ሙስናን ለመከላከል የሥነ ምግባርን ደንብ ማክበር፣ ሙያዊ ብቃትን ማሳደግ፣ ግልጽነትን ማረጋገጥ፣ ሕዝብን ማሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ ሙስና ለሀገራት ችግር መኾኑን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ሙስናን የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ነገር ግን አሁንም ችግሮች እንዳሉ ነው ያመላከቱት። የጸረ ሙስናን ቀን ከማክበር ባለፈ ሙስናን መታገል ይገባል ነው ያሉት።

የተቋማቸውን አሠራር ለማዘመን የሪፎርም ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል። ተቋማቸው ለሙስና ተጋላጭ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ለሙስና በር የሚከፍቱ አሠራሮችን መዝጋት እና በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። ማኅበራትን ኦዲት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። ማኅበራት አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ መሥራታቸውንም አመላክተዋል። በኦዲት ጉድለት የሚገኝባቸውን የማስተካከል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ለባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ፈትኗቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን በራስ ኀይል ለማስከበር የራስን አቅም መገንባት ይገባል” ጎሹ እንዳላማው
Next article“በቀጣይ የሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ