“ሰላምን በራስ ኀይል ለማስከበር የራስን አቅም መገንባት ይገባል” ጎሹ እንዳላማው

58

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ምልምል የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላት ለተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና ዛሬ መስጠት ጀምሯል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በክልሉ እና በከተማ አሥተዳደሩ የሰላም እጦት አጋጥሞ በአስቸኳይ አዋጅ እየተመራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ክልሉን ቀጥሎም ሀገርን ለማፍረስ የተጠነሰሰውን መጠነ ሰፊ ሴራ በጥምር የጸጥታ ኀይላት እና በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል። አሁን ላይም የሰላም ኹኔታው በየቀኑ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ እና ሁሉም አካባቢ እየተረጋጋ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል። መንግሥታዊ ኀላፊነቶችን በብቃት እየተወጣን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ሥልጠና ሠጥቶ በየቀበሌው በማሰማራት የተገኘውን ሰላም የበለጠ መሠረት ለማስያዝ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የራስን ሰላም በራስ ኀይል ማስከበር እንዲቻል የራስን አቅም መገንባት እንደሚገባ እና ይህንንም ለማድረግ ሥልጠናው ወሳኝ እንደኾነ አስገንዝበዋል። አሁን የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ከአካባቢው ማኅበረሰብ የተውጣጣ ኀይል ሠልጥኖ እና ታጥቆ ሕግን የሚያስከብር ኀይል ዝግጁ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

ለዚህም ከከተማዋ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተመለመሉ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላትን ማሠልጠን እንደተጀመረ ነው ያስረዱት፡፡

በሥልጠናው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ የፖሊስ ሠራዊት አዛዦች እና የከተማዋ ሥራ አሥፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብዝኅነት በአግባቡ ከተስተናገደ ለሀገራዊ መግባባት እና ለኅብረ ብሔራዊነ አንድነት መሠረት ነው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
Next articleየጸረ ሙስና ቀን በዓልን ከማክበር ባለፈ በቁርጠኝነት ሙስናን መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ።