
ጎንደር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር እየተከበረ ነው። በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ብኅሐነት ለልዩነት ምንጭ እንዲኾን ባለፉት ጊዜያት ሲቀነቀን መቆየቱን ተናግረዋል። የተቀነቀነው ልዩነት ለሀገር አንድነት ፈተና ኾኖ ቆይቷል ያሉት አፈ ጉባኤው ለችግሮቹ መፍትሄ ለማበጀት መሰብሰብ፣ መወያየት፣ መመካከር እና መግባባት ይገባል ብለዋል።
“ብዝኅነት በአግባቡ ከተስተናገደ ለሀገራዊ መግባባት እና ለኅብረ ብሔራዊነ አንድነት መሠረት ነው” ያሉት አፈ ጉባኤው አብሮነት በመተሳሰብ እና በመቻቻል የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚቻልበት መንገድ መኾኑን አንስተዋል። አብሮነት የጋራ ራዕይ ያላቸው ማንነቶች የሚፈጥሩት የመስተጋብር ውጤት መኾኑንም ገልጸዋል።
የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ እንቅስቃሴ መደረጉንም አንስተዋል። እውነተኛ ዲሞክራሲን ለመገንባት የሃሰት ትርክትን በማስወገድ የወል ትርክት እንዲኖር እና አንድነትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ባለመግባባት ምንክያት የጋራ ቤታችን ፈርሶ ሀገር አልባ እንዳንኾን ሁላችንም ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን አንድ በሚያደርጉን እና በሚያስማማን ገዥ ሃሳብ ላይ ብቻ እንድናተኩር አደራ እላለሁ ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባት የበኩሉን ጉልህ ድርሻ መወጣቱንም አፈ ጉባኤው አንስተዋል። በቅርቡ ፍላጎትን በኃይል ለማስከበር በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳያቀኑ በክልሉ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል። የፌደራል መንግሥት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ በትኩረት እየሠራ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው የጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ጎንደርን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ የፌደራል መንግሥት በቢሊዮን ብሮች መድቦ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ገልፀዋል። የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ታላላቅ እቅዶችን በመያዝ ጎንደር እና አካባቢዋን ለማልማት በትኩረት እንደሚሠራም ገልፀዋል። የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች ይበልጥ የሚጠናከሩት ሰላም ሲኖር ነው ያሉት አፈ ጉባኤው በአካባቢው ታጥቀው የሚገኙ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የከተማዋ ሕዝብ እና የሃይማኖት አባቶች የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት በመልእክታቸው።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!