“የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከ33 በመቶ በላይ የእናቶችን ሞት ይቀንሳል” አብዱከሪም መንግሥቱ

24

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእናቶች ላይ የሚደርሰውን ሞት ለመቀነስ ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱከሪም መንግሥቱ እንዳሉት ሀገሪቱ መከላከል እና ማከምን ማዕቀፍ ያደረገ የጤና ፖሊሲ እየተገበረች ትገኛለች። ፖሊሲው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ የእናቶችን፣ የወጣቶችን፣ የአፍላ ወጣቶችን እና የሕጻናትን ጤና አገልግሎት ማሻሻል ዋነኛ አቅጣጫ ኾኖ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ደግሞ የችግሩ ዋነኛ መፍትሄ መኾኑን ገልጸዋል። የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከ33 በመቶ በላይ የእናቶችን ሞት የሚቀንስ አሠራር መኾኑንም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በቤተሠብ ዕቅድ ላይ በተሠራው ሥራ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የእናቶች፣ የሕጻናት እና ወጣቶች ሞት ችግር መኾኑን ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ወጣቶች ላልተፈለገ እርግዝና እንዲጋለጡ አድርጓል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም እንደ ክልል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። በቀጣይም የረጅም ጊዜ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን የሚጠቀሙ እናቶችን እና ወጣቶችን ቁጥር ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሴቶች ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ዕቅዱ እንዲሳካ ሊያግዙ ይገባል ብለዋል። ጤና ሚኒስቴር የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ እና ግብዓቶችን በተሟላ መንገድ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል። የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ የነባር እና አዲስ ሚሊሻ አባላት ስልጠና ተጀምሯል።
Next article“ጎንደር የቀደመውን ከፍታ ጠብቃ እና የገጠማትን ችግሮች ፈትታ መቀጠል ይገባታል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)