
ጎንደር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ምልዕክት 19ኛው የብሔር ብሔርሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ስዓዳ አብዱረህማን፣ የአፋር ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አሲያ ከሚል፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታየ ከበደ እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች እና የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ዋና አፈ ጉባኤ እናትነሽ ዋለ የአብሮነት ተምሳሌት የኾነውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ለማክበር በጎንደር ከተማ ለታደሙ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ የኮሪደር ልማት፣ የመገጭ ግድብ ግንባታ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መኾኑን የተናገሩት ዋና አፈ ጉባኤ እናትነሽ የብሔረሰቦችን አድነት በማጠናከር የሀገሪቱን አንድነት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ “የሁሉ እናት ወደ ኾነችው ጎንደር ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ” ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዘር፣ ብሔር እና ሃይማኖት ባለመለየት ጎንደር ለሀገር አንድነት ጉልህ ሚና መወጣቷን አስታውሰው “እንደ ሀገር አንዳችን ለአንዳችን መኖር ከቻልን የአፍሪካን ልዕልና ማስቀጠል እንችላለን” ብለዋል። የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓል ስናከብር የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስቀጠል ሊኾን ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“በጎንደር ቆይታችሁ የአባቶቻችሁን ድንቅ የታሪክ አሻራ ቅርሶችን እንድትመለከቱ” ሲሉም እንግዶች በጎንደር ቆይታቸው የቱሪስት መስህቦችን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው በቀጣይ የ20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በጎንደር ከተማ እንዲከበርም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!