በአማራ ክልል በቀጣዩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያልተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሥራዎች ይከናወናሉ።

37

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በአማራ ክልል በወረዳ ደረጃ ተሳታፊዎችን የሚያስመርጡ ከሁለት ሺህ 200 በላይ ተባባሪዎችን የማሠልጠን ሥራ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። በክልሉ ብዙ ወረዳዎች የተባባሪ አካላት ተሳታፊዎችን በመለየት አስመርጠዋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ በቀጣዩ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቀሪ የምክክር ሥራዎችን ለማካሄድ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሠባሠብ እና ለዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት ላይ መኾኑን ያመላከቱት ዋና ኮሚሽነሩ ሥራው በዘጠኝ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች መጠናቀቁን አውስተዋል፡፡ ከታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ እና ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከ350 በላይ ወረዳዎች ከሚመጡ ከ7 ሺህ 700 በላይ ተሳታፊዎች እና ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን የክልሉን አጀንዳ የማሠባሠብ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጻ ቀሪ ዐበይት ሥራዎች የፌዴራል ባለድርሻ አካላትን በመሠብሠብ አጀንዳ እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት አጀንዳቸውን እንዲልኩ እና በሚሰጣቸው ቀመር መሠረት ተሳታፊዎችን እንዲልኩ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሥራውን 80 በመቶ የተሟላ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ትግራይ ክልል በመሄድ አንዳንድ ባለድርሻ አካላትን ማነጋገሩን አስታውሰው በክልሉ በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋርም ጥሩ የሚባል ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ኮሚሽኑ ከክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ለመነጋገር በዝግጅት ላይ መኾኑን ገልጸው በክልሉም በኩል ምላሹ መልካም መኾኑን አብራርተዋል፡፡

በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ እና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር አብረው መሥራት ላልጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጥሪ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ሁኔታ እንደሚያስቀምጡ እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ በኮሚሽኑ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የሚያቀርቡት ምክንያት አሳማኝ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ ኮሚሽኑ አሁን ላይ ከ50 በላይ ከሚኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየሠራ እና የሚሠራውን ሥራ ፓርቲዎቹ እየተመለከቱ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ሁሉንም ማሳተፍ ስላለበት በትጥቅ ትግል ላይ ካሉ አካላት ጋር ቅርበት ሊኖራቸው ከሚችሉ የውጭም ኾነ የሀገር ውስጥ አካላት በኩል ለማግኘት በተቻለ መጠን አሁንም ጥረት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትም ሁሉም በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፍ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየብቸና ከተማ አሥተዳደር ለግል ታጣቂዎች ሥልጠና መስጠቱን ገለጸ።