የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።

40

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ባዩሽ አጥናፋ እና ወይዘሮ አያል መኮንን በደብረ ማርቆስ ከተማ የዓለም ኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን እያከበሩ ነበር ያገኘናቸው። “ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ” በማለት እያስተማሩ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ናቸው።

በጎ ፈቃደኞቹ የሕይዎት ተሞክሯቸውን በማካፈል ኅብረተሰቡ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይኾን እያገለገሉ ቢኾንም ትምህርቱን ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ክፍተት መኖሩን አውስተዋል።

ትውልዱ ከእኛ ሊማር ይገባል ያሉት በጎ ፈቃደኞቹ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ እና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖችም ሌሎችን በማስተማር የዜጎችን ሕይዎት ሊታደጉ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሌሎች የኤች አይቪ ኤድስ ቀንን ሲያከብሩ ያገኘናቸው ተሳታፊዎችም የግል እና የመንግሥት ተቋማት ኤች አይ ቪ ኤድስን የመከላከል ሥራ ከሌሎች ሥራዎች ጋር በማቀናጀት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጤና ትምህርቶችን ተደራሽ በማድረግ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ በትኩረት ከተሠራ የበሽታውን ስርጭት መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሃብቴ ወርቁ በከተማ አስተዳደሩ በሽታውን ለመከላከል እየተሠራ ቢኾንም አሁንም የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በየዓመቱ ከማክበር ባለፈ የሁልጊዜ ተግባር በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ እንደሚሠራም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን “ሰብዓዊነትን ያከበረ የኤች አይቪ ኤድስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በፓናል ውይይ ተከብሯል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሥተዳደራዊ ቅሬታዎችን በአደባባይ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ወደ ሌሎች ከተሞች መስፍት አለበት።
Next articleበአማራ ክልል በቀጣዩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያልተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሥራዎች ይከናወናሉ።