አሥተዳደራዊ ቅሬታዎችን በአደባባይ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ወደ ሌሎች ከተሞች መስፍት አለበት።

46

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች እና ተገልጋዮች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ያለውን ሥራ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውበቱ አለ ተገኝተዋል፡፡

በደሴ ከተማ አሥተዳደር በየደረጃው ባሉ የከተማው መዋቅሮች የሚነሱ አሥተዳደራዊ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ችግሮች ተገልጋዮች እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት መሪዎች በሚገኙበት በአደባባይ መድረክ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መኾኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳቱ የመድረኩን ስያሜ ማስተካከለልን ጨምሮ አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ወደ ሌሎች ከተሞች ሊሰፋ የሚችል እንደኾነም ነው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በኾነ መንገድ መሠራት ያለበት መኾኑ በሕገ-መንግሥት ጭምር የተቀመጠ መርህ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ይህንን መርህ መሠረት በማድረግ የከተማው ነዋሪዎች እና ተገልጋዮች ቅሬታቸውን የከንቲባ ችሎት በሚል በተሰየመው የአደባባይ መድረክ እየቀረቡ አሥተዳደራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት መልካም አሥተዳደርን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

አሠራሩ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ጉዳዮችንም በመቀነስ የፍርድ ቤት እና የሌሎች ፍትሕ ተቋማትን የሥራ ጫና የሚያቃልሉ ብሎም የዜጎችን እንግልት የሚቀንሱ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኾኖም የተፈለገውን ውጤት በአግባቡ እንዲያሳካ ለማስቻል የከንቲባ ችሎት ከሚለው ስያሜው ጀምሮ የአሠራር ማስተካከያዎች ሊደረግበት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ “የከንቲባ ችሎት” በሚል በመሰየሙ ምክንያት ተገልጋዮች እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመቁጠር በፍርድ ቤቶች በክርክር ላይ ያሉ ጉዳዮችን ጭምር በብዛት ይዘው እየመጡ በመኾኑ ስያሜው መስተካከል አለበት ነው ያሉት፡፡ በመደበኛ ፍርድ ቤት በክርክር ላይ ያሉ ጉዳዮች በዚህ መድረክ መታየት የማይችሉ ናቸውም ብለዋል። በመድረኩ የሚሰጡ መፍትሔዎች የአሥተዳደር ፍትሕን የሚያረጋጡ አሥተዳደራዊ ውሳኔዎች በመኾናቸው በአሥተዳደር ተቋማት በራሳቸው ተግባራዊ የሚኾኑ ናቸው።

እንደ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተቆጥረው ውሳኔዎችን መደበኛ ፍርድ ቤት የሚያስፈጽማቸው አለመኾናቸው ለተገልጋዮች ግልጽ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ መድረኩ የዜጎችን ቅሬታ ግልጽ በኾነ የአሠራር ሂደት ለመፍታት እና መልካም አሥተዳደርን ለማስፈን ካለው ፋይዳ በተጨማሪ የፍርድ ቤቶች እና የሌሎች የፍትሕ ተቋማትን የሥራ ጫና የሚቀንስ በመኾኑ የአሠራር ሥርዓት ተቀርጾ ሊሠራ እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም አሠራሩ የማኅበረሰቡን ችግር በአፋጣኝ ለመፍታት እና ለፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ መኾኑን ገልጸው አሠራሩ እንዲጠናከር በጋራ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የአሥተዳደር ፍትሕ የሚሰጥበት መድረኩ የደሴ ከተማን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጉዳዮች እና በአገልግሎቱም የበርካታ አቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ችግሮችን እየፈታ ያለ ስለመኾኑ ነው የገለጹት፡፡

ወደፊትም ከፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት በስፋት እና በተጠናከረ መንገድ በማስቀጠል አሥተዳደራዊ ኀላፊነትን እንደሚወጡ ገልጸው የፍትሕ አካላቱ አሠራሩን አይተው ለሰጡት ግብዓት እና ለማገዝ ላሳዩት ተነሳሽነት ምሥጋና ማቅረባቸውን ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክልላዊ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ ዝግጅት ላይ ለመታደም የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል መሪዎች ጎንደር ከተማ ገቡ።
Next articleየኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።