የኮሪደር ልማቶች አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎችን በተመሳሳይ ቀለም ለማስዋብ እየተሠራ ነው።

57

ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሕንፃ ሹም ጽሕፈት ቤት አሥተባባሪነት የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ከፍ በማድረግ በኩል ሰፊ ድርሻ ያለው የሕንፃ የውጭ መለያ ቀለም የተዘጋጀ ጥናት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል። የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሕንፃ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደረጀ ንጉሴ ባሕርዳር በተፈጥሮ የታደለች ድንቅ የውበት እና የመስህብ ሃብቶች ባለቤት መኾኗን ተናግረዋል።

ከተፈጥሮ ውበቶቿ ባሻገር ሰው ሠራሽ ዘመን ተሻጋሪ እና ማራኪ ገጽታ ያላቸው የአሥተዳደር፣ የሆቴል እና ቱሪዝም፣ የመኖሪያ እና ሌሎች ሕንፃዎችን የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የኮሪደር ልማቱን ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ የሕንፃዎችን የውጭ ገፅታ ብራንድ ገላጭ እና ቋሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተሻገር አዳሙ ለስማርት ባሕርዳር ስኬት ከ22 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማቶች ግንባታ ደረጃ በደረጃ ለይቶ ማልማት ተጀምሯል ብለዋል። በመጀመሪያው ዙር የተጀመረው የሦስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በጥሩ ሂደት ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

ለስማርት ባሕርዳር በሚገነቡ የኮሪደር ልማቶች አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎች በተመሳሳይ ቀለም መዋብ የከተማዋን ተመራጭነት ይጨምራሉ ነው ያሉት። የኮሪደር ልማቱ ውበት ትልቁ መገለጫ የኾኑት ሕንጻዎች የተዘበራረቀ እና ስሜት በማይሰጡ ቀለሞች የተቀቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማቱ አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎችን የባለንብረቶችን ፍላጎት እና ጥቅም ባከበረ መልኩ ኮድ ያለው ተመሳሳይ በኾነ ብራንድ ቀለም ተውበው የከተማዋን ተመራጭነት ማሳደግ እንዲችሉ ተደርጎ ይሠራል ነው ያሉት።

ከባሕርዳር ከተማ ኮሙዩንኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የቀረበውን ጥናት መርምሮ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ አካላት ከምንጊዜም በላይ ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል።
Next article19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በአማራ ክልል የማጠቃለያ ዝግጅት በጎንደር ከተማ ይከበራል።