የፍትሕ አካላት ከምንጊዜም በላይ ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል።

30

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችሉ ቅንጅታዊ አሠራሮች ላይ መክረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የአሠራር ብልሹነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በፍትሕ እና በዳኝነት አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይ ኅብረተሰቡ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸር አድርጎታል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ እና ማረሚያ ቤቶች ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት የተቀዛቀዘውን ቅንጅታዊ አሠራር ከምንጊዜውም በላይ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የፍትሕ ተቋማትን በማጠናከር የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ መመለስ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መኾኑን አመላክተዋል፡፡

የፍትሕ ሥርዓትን ማስተካከል ሌሎች የልማት የዴሞክራሲ እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ አበበ አወቀ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

ኅብረተሰቡን ያማረሩ እና ዕምነት ያሳጡ ችግሮችን በመለየት የፍትሕ አሰጣጡን ለማሻሻል እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ባዬ ጌታቸው ናቸው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ልጅ አዱኛ ሙሉጌታ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር የወንጀል ምርመራን በአግባቡ በመፈጸም አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ከማድረግ አንጻር ማነቆ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ያለውን የሰው ኀይል በማቀናጀት ለፍትሕ ሥራው አጋዥ ለመኾን በትኩረት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ታሪኩ ዳኜ የሕግ ታራሚዎች በቀጠሯቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ከማድረግ ጀምሮ ፍትሕን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከፍትሕ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡

በመድረኩ የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት በፍትሕ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል የስምምነት ቻርተርም ተፈራርመዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መሥራት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።
Next articleየኮሪደር ልማቶች አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎችን በተመሳሳይ ቀለም ለማስዋብ እየተሠራ ነው።