
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። የምክር ቤት አባላቱም ለንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ጥያቄዎችን አንስተዋል። ሚኒስትሩም ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምክር ቤት አባላቱ የምርት አቅርቦት ምሕዳሩን ለማስፋት እየተሠራ ያለው ሥራ ምን እንደኾነ ጠይቀዋል። አምራች እና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን ማስፋት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት መቆጣጠር ይገባልም ብለዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረጉ መኾናቸውም ገልጸዋል። ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪዎችም ሕዝብን ለመስቅልቅል ሕይወት እየዳረጉት ነው ብለዋል። ሕጋዊ ነጋዴዎች በሕገወጥ ነጋዴዎች እና በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ምክንያት ከግብይት ሥርዓቱ እየወጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በኑሮ ውድነት ምክንያት ልጆቻችን ምን እናብላ የሚሉ ድምጾች መበራከታቸውንም አንስተዋል። የኑሮ ውድነት በዚህ ከቀጠለ ሀገሪቱ ወደ ውስብስብ ችግር እንደምትገባም አስገንዝበዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) የዋጋ ግሽበት እየቀነሳ እና አውንታዊ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ተናግረዋል። የኑሮ ውድነቱ ጫና ያሳደረባቸው ቋሚ ገቢ ባላቸው ወገኖች ላይ መኾኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ችግሩን ለማቃለል መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የደሞዝ ማሻሸያ ማድረጉንም ተናግረዋል።
የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የምርት አቅርቦትን የመጨመር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የምርት አቅርቦቱን ከመጨመር ጎን ለጎን የገበያ ሥርዓቱን በአግባቡ ለመምራት እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ የገበያ ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በተሠራው ሥራ ከ105 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል።
የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት ከ29 ነጥብ 2 በመቶ 19 በመቶ ዝቅ ማለቱንም ገልጸዋል። በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 134 የቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች እንዲሠፉ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ የንግድ ማዕከላት ሚና ከፍ ያለ መኾኑንም ተናግረዋል።
የምርት ነጻ ዝውውርን የሚገቱ፣ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን የሚገድቡ 283 ሕገ ወጥ ኬላዎች በመላ ሀገሪቱ ተንሰራፍተው እንደሚገኙም ገልጸዋል። የቀረጥ እና ታክስ ጉዳይ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። ኬላ ይነሳ ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ቢወሰንም የተለያዩ ሰበቦች እየተፈለጉ ሕገ ወጥ ኬላዎች በመላ ሀገሪቱ እንደተንሰራፉ ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ ኬላዎች የምርት ነጻ ዝውውር እና የሎጂስቲክስን ቅልጥፍናን የሚገድቡ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያላቸው መኾኑንም አመላክተዋል። ኬላዎች እንዲነሱ ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውንም ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት ወራት መሠረታዊ ሸቀጦች ሲቀርቡ የነበሩት በመንግሥት ሳይኾን በግሉ ሴክተር እንደነበርም አስታውሰዋል። በተለይ በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት 208 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ ወደ ሀገር ገብቶ ገበያውን እንዳረጋጋ መደረጉን ነው ያነሱት።
ኅብረተሰቡ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የግብይት ማዕከላት ላይ ምርት እንዲገዛም አሳስበዋል። በቂ ሼድ ያላቸው የምርት ጥራት የሚጠበቅበት የግብይት ማዕከላት በሁሉም ክልሎች እየተገነቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በሕገወጥ ደላላዎች ላይም እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!