
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲያከናውናቸው በሕግ ከተሰጠው ተግባር ውስጥ የሥነ ምግባር ግንባታ፣ የተቋም የአሠራር ሥርዓት ጥናት እና የሃብት ምዝገባ እና ማጣራት ሥራዎች ይገኙበታል። ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው የሰላም ችግር ምክንያት በተቋማቱ የታዩ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ለመፍታት የለውጥ ሥራዎች መጀመራቸውን የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ገልጸዋል።
የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በክልሉ በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት በሙሉ አቅም ለመተግበር አሁንም ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት። ከሚከናወኑት ሥራዎች መካከል ደግሞ የጸረ ሙስና ቀን አንዱ ሲኾን “ወጣቶችን ያማከለ የጸረ ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እስከ ኅዳር/2017 ዓ.ም መጨረሻ የሚቆይ የጸረ ሙስና ቀን እንደሚካሄድም ነው ያስገነዘቡት።
በመርሐ ግብሩ “ሥነ ምግባር የተሞላበት አገልግሎት አሠጣጥ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በመከላከል የመንግሥት ተቋማት መሪዎች እና የባለሙያው ሚና” በሚል በተዘጋጀ ሰነድ ዙሪያ ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል። የመንግሥት ተሿሚዎች፣ ተመራጮች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል። የስፖርታዊ ውድድሮች፣ የጽዳት ዘመቻ እና ሌሎች ሥራዎችም እንደሚከናወኑ ነው ያብራሩት።
ሙስና ዓለም አቀፍ ወንጀል መኾኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ማኅበረሠቡ ተገንዝቦ ለጸረ ሙስና ትግሉ አጋዥ እንዲኾንም ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን ተገቢ ያልኾነ አባባል በመጸየፍ “ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን እሳቤ ባሕል ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።
በሥነ ምግባር ግንባታ እና በጸረ ሙስና ትግሉ የሃይማኖት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ ተቋማት እና የሲቪክ ማኅበራት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በተለይም ደግሞ ወጣቶች በሥነ ምግባር ተገዥ ኾነው ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል የሀገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!