
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ውብሸት ወልደ ሚካኤል በሰሜን ሸዋ ዞን ባሶ እና ወራ ወረዳ አባ ሞቴ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፤ አርሶ አደሩ በምርት ዘመኑ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና አተር መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርቱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይረግፍ እና እንዳይበላሽ የደረሱ ሠብሎችን በጥንቃቄ እየሠበሠቡ እንደኾነ ነው የሚገልጹት፡፡
የተሠበሠበው ምርት በአግባቡ እየተከመረ መኾኑን የገለጹት አርሶ አደሩ ወቅተው ጎተራ እስኪያስገቡ ድረስ እንዳይባክን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩ፡፡ አርሶ አደሩ ካመረቱት ምርት 40 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡ ልክ እንደ አርሶ አደር ውብሸት ወልደ ሚካኤል ሁሉ በቀጣናው ያሉ ሰፋፊ የእርሻ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ኮምባይነርን በመጠቀም ለመሠብሠብ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ነው አሚኮ ያረጋገጠው፡፡
በሰሜን ሽዋ ዞን 23 ወረዳዎች በ549 ሺህ 601 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሠብሎች በዘር ስለመሸፈኑ የሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና መምሪያ የሠብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ292ሺህ 889 ሄክታር መሬት በላይ የተለያዩ የደረሱ ሠብሎችን መሠብሠብ እንደተቻለም ቡድን መሪው አስገንዝበዋል፡፡
በዞኑ 103 ሺህ 232 ሄክታር መሬት የሚጠጋ ሠብል እንደተወቃ እና 2 ሚሊዮን 259 ሺህ 900 ኩንታል ምርት እንደተገኘም ነው የተገለጸው፡፡ አሁን ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ የዝናብ ኹኔታ ከብሔራዊ ሜትዮሮሎጅ ኤጀንሲ በደርሰ ጥቆማ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ሙሉ በሙሉ የሚጠበቀውን ምርት ያለብክነት ለማግኘት መረጃውን እስከ ታች ድረስ በማውረድ በሁሉም አካባቢዎች ዘመናዊ የእህል መሠብሠቢያ ኮምባይነርን በመጠቀም ከብክነት በጸዳ መልኩ እንዲሠበሠብ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሰፋፊ ምርት ባሉባቸው ወረዳዎች የእህል መሠብሠቢያ ማሽኖችን በመከራየት እና የአካባቢውን ባለሃብቶች በማስተባበር የመሠብሠብ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የዝናብ ኹኔታ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል የብሔራዊ ሜትዮሮሎጅ ኤጀንሲ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በዚህም አርሶ አደሩ የደረሱ ሠብሎችን ፈጥኖ መሠብሠብ እንዳለበት በተዋረድ ያለው የግብርና ባለሙያ መረጃዎችን በማድረስ እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ መኾኑንም ነው የተናገሩ፡፡ ሠብል ማሠባሠብ ብቻ ግብ አይደለም ያሉት ቡድን መሪው የተሠበሠበው ምርት ከመሬት ከፍ ብሎ እና በአናት በኩል ዝናብ እንዳይገባው ከላይ ላስቲክ በማልበስ መሸፈን እንደሚገባም አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የድህረ ምርት ቴክኖሎጅ ባለሙያ ምትኩ መላኩ በምርት ዘመኑ ከ167 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ነው ያብራሩት፡፡ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኗል ያሉት ባለሙያው ከተዘራው ከ52 በመቶ በላይ የሚኾነው ምርት መሠብሠቡንም ተናግረዋል፡፡
ቀሪ ያልደረሱ እና ያልተሠበሠቡ ምርቶች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ በወቅቱ ሠብሉን እንዲሠበሥብ የባለሙያ ምክረ ሃሳብ እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ባለሙያው አርሶ አደሩ ከልማዳዊ አሠራር ተላቆ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ምርቱ ሳይባክን እንዲሠበሥብ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሰፋፊ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች በኪራይ እና በባለሃብቶች ትብብር ምርቶቻቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም እየሠበሠቡ መኾኑንም ነው ያብራሩ፡፡ የተሠበሠበውን ምርት ዝናብ እንዳያበላሸው ቶሎ በመውቃት ወደ ጎተራ እንዲያስገቡ በተዋረድ ሥራ እየተሠራ መኾኑም ነው የተገለጸው፡፡
ምርቱ ከተወቃ በኋላም በተባይ እንዳይጠቃ ዘመናዊ ጆንያዎችን እና ዘመናዊ የብረት ጎተራዎችን በመጠቀም ከብልሽት በጸዳ መልኩ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ምርት እንዳይባክን ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ቴክኖሎጅን መጠቀም በመኾኑ በክልሉ ምርታማ የተባሉ ዞኖች ቴክኖሎጅን በመጠቀም ምርታቸውን እየሠበሠቡ መኾናቸውን ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት ከመሠብሠብ ጀምሮ እስከ ማከማቸት ያሉ ሂደቶችን በባለሙያ እና በቴክኖሎጅ በመታገዝ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የምርት መባከን በእጅጉ እንደሚቀንስ እና የታቀደው 167 ሚሊዮን 303 ሺህ 819 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ነው ያብራሩት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!