በደብረ ማርቆስ ከተማ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ እየተሠራ ነው።

47

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በከተማዋ ከሚገኙ መምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞች ጋር በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት አካሂዷል። በደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 47 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ የመማር ማስተማር ሥራ እያከናወኑ የሚገኙት 29 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው።

የዛሬው ውይይትም እስካሁን ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ የሚያስችል ነው። ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን የማካካስ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን መምህራኑ ተናግረዋል። ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ወላጆች የበኩላቸውን ኀላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ በከተማ አሥተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ እየሠራን ነው ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሽ ተመስገን ሀገር ተረካቢ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ማየት እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ዜጋ ትልቅ ውድቀት መኾኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል። ችግሩን ለመቀልበስ በተለይ መምህራን በኅላፊነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በሕጻናት፣ አረጋዊያን እና ሴቶች ዙሪያ እየተሠሩ ባሉ መልካም ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መከሩ፡፡
Next articleሠብልን ከብክነት መከላከል