
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቀለብ የመስጠት ግዴታ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሠብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 በግልጽ ተቀምጧል። በዚህ ጉዳይ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ያገኝ ዘንድ በማሰብ ከሕግ ባለሙያ ጋር ቆይታ በማድረግ አጭር መረጃ አስቀምጠናል።
ጋዜጠኛው ከጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ፍስሐ ሲሳይ ጋር የነበረውን አጋርተናችኋል።
ጋዜጠኛው፡- በሕግ ዐይን ሲታይ ቀለብ ምንድን ነው? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- ቀለብ ማለት በጥሬ ትርጉሙ ምግብ ማለት ቢኾንም በሕግ ዐይን ሲታይ ግን ተጨማሪ ጉዳዮችንም ያካትታል፡፡ ከሕግ አኳያ የቀለብን ትርጓሜ ስንመለከት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 መሠረት ቀለብ ማለት ለቀለብ ተቀባዩ የምግብ፣ የልብስ፣ የመኖሪያ፣ ጤናውን የሚጠብቅበት እና እንደ ኹኔታው ለትምህርት አስፈላጊውን ወጭ የሚሸፍንበት ገንዘብ መስጠት ወይም መቁረጥ ነው።
ጋዜጠኛው፡- ቀለብ የመቀበል መብት ያለው ማን ነው? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- ቀለብ የሚሠጠው በዋነኛነት ከ18 ዓመት በታች ለኾኑ የቀለብ ወጭ የመጠየቅ መብት ያላቸው ሲኾን ቀለብ የመጠየቅ መብት ግን በልጆች ብቻ ተገድቦ የተቀመጠ አይደለም። በዕድሜ መግፋት፣ በጤና ችግር ምክንያት ሠርቶ ራሱን ማሥተዳደር ያልቻለ የቤተሠብ አባል በቤተሠብ ሕጉ መሠረት ቀለብ የመጠየቅ መብት አለው፤ ።
ጋዜጠኛው፡- ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበትስ ማን ነው? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው በቀጥታ ወላጆች ናቸው። ወላጆች በተለያየ ምክንያት አብረው ሊኖሩ ወይም ሊለያዩ ይችላሉ። በወላጆች መለያየት ልጆች ችግር ላይ እንዳይወድቁ ቀለብ ባል ወይም ሚስት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ይኖራል፡፡ ባል/አባት ወይም ሚስት/እናት የገንዘብ አቅም ባይኖራቸው አቅም ወይም በቂ ሃብት ካላቸው ወንድም ወይም እህት ወይም አያት ከእነዚህም ሲያልፍ አክስት ወይም አጎት ለልጆች ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የቤተሠብ ሕጉ በግልጽ አስቀምጧል።
ከልጆች ባሻገር በዕድሜ መግፋት አልያም በጤና ችግር ምክንያት ሠርቶ ራሱን ማሥተዳደር ያልቻለ የቤተሠብ አባል ስለመቸገሩ በቂ ማስረጃ አቅርቦ የመርዳት አቅም ወይም ሃብት ካለው የቤተሠብ አባል ቀለብ የመጠየቅ መብት አለው፤ የተጠየቀው የቤተሠብ አባልም ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለበት።
ጋዜጠኛው፡- የቀለብ መጠን እንዴት ይወሰናል? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- በቤተሠብ ሕጉ በአንቀጽ 202 በአጭሩ እንደተቀመጠው የቀለብ መጠን የሚወሰነው የቀለብ ተቀባዩን ችግር እና የቀለብ ሰጭውን አቅም በማመዛዘን ነው። ቀለብ ሰጭው የራሱን ሕይዎት ለመምራት አንድም ችግር ላይ ከኾነ አልያም በተወሰነበት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ሲመራው የነበረ ሕይዎት ቀውስ እንዳይገጥመው የቀለብ መጠኑ በጥንቃቄ ይወሰናል። የቀለብ ወጭውም ለቀለብ ተቀባዩ በገንዘብ ይሰጣል፡፡
ጋዜጠኛው፡- የፍርድ ቤት ውሳኔው አተገባበር በምን መልኩ ነው ክትትል የሚደረግበት? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል። ቀለብ ተቀባዮቹ ልጆች ቢኾኑ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መሠረታዊ ፍላጎታቸው እየጨመረ ይሄዳል።
ከዓመታት በፊት የተወሰነላቸው ቀለብ በአሁኑ ወቅት በቂ ላይኾን ይችላል። ቀለብ ተቀባዩ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ቀደም ሲል ውሳኔ ያገኘውን ፋይል እንደገና ማስከፈት ይችላል። ቀለብ ተቀባዩ ተጨማሪ ቀለብ የሚወሰንለት ቀለብ ሰጭው ቀለብ ለመጨመር የተሻለ ሃብት መፍጠሩ ከተረጋገጠ ብቻ ነው።
ጋዜጠኛው፡- ቀለብ ተቀባዩ ቀለብ የመቀበል መብቱን የሚያጣበት ጉዳይ ይኖር ይኾን? አቶ ፍስሐ ሲሳይ (ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ) ፡- በቤተሠብ ሕጉ አንቀጽ 200 እንደተቀመጠው ቀለብ ተቀባዩ በቀለብ ሰጭው ወይም በዚህ ሰው ወደ ላይ እና ወደ ታች በሚቆጠሩ ቤተሰቦቹ ሕይዎት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈፀመ ወይም ለመፈፀም የሞከረ እንደኾነ ቀለብ የመቀበል መብቱን ያጣል።
ሌላው ልጆች 18 ዓመት ከሞላቸው እንዲሁም ችግር ላይ ወድቆ ቀለብ የተቆረጠለት ሰው ከችግሩ መውጣቱ ከተረጋገጠ ቀለብ የመቀበል መብቱን ያጣል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!