
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ቢሮ ከሕዝብ ግንኙነት፣ ከሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በዋናነት ደግሞ ውይይቱ የወባ በሽታ ላይ ያተኮረ ነበር።
የመድረኩ ዓላማም የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት የጀመሯቸውን ሥራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው።
እንደ አማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ በክልሉ ከሐምሌ 01/2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም ፦
👉2 ሚሊዮን 569 ሺህ 290 የወባ ሕሙማን ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
👉1 ሚሊዮን 95 ሺህ 127 ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸው ታክመዋል።
👉የዚህ በጀት ዓመት የወባ ህሙማን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 440 ሺህ 548 ወይም 67 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ አለው።
በተጠቀሰው ጊዜም በክልሉ፦
👉የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር
👉የጃቢጠኽናን
👉የአየሁጓጉሳ
👉የደራና
👉የጓንጓ ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ናቸው። ከተጠቀሱት አካባቢዎች የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ደግሞ በስርጭቱ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ይህም ክልሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ በወባ በሽታ ታማሚ ቁጥር ብዛት ሁለተኛ አድርጎታል።
በክልሉ የወባ በሽታ ሥርጭት ከፍተኛ በኾነበት በባሕር ዳር ከተማ ያነጋገርናቸው እናት በሽታው በቤተሰባቸው ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሲገልጹ “የወባ በሽታ ቤተሰቤን ከማጎሳቆሉ በላይ ኑሮዬን ከድጡ ወደማጡ አድርጎብኛል” ብለዋል። የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ዓለምአንች ይርዳው በጉልት ገበያ ንግድ ተሠማርተው ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። የወባ በሽታ በዚህ ዓመት በተለየ ሁኔታ በአካባቢያቸው እንደተከሰተና እሳቸውን ጨምሮ ሁለት ልጆቻቸው በወባ በሽታ መያዛቸውን ነግረውኛል። በጉልት ገበያ ንግድ በሚያገኟት ገቢ ቤተሰብ የሚመሩት እናት በወባ በሽታ ያለቻቸውን ጥሪት ለህክምና በማዋላቸውና የንግድ ሥራውም በማቆሙ የከፋ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል። እሳቸው አገግመው ወደ ሥራ ሲመለሱም ልጆቻቸው በመታመማቸው የንግድ ወረት ጥሪታቸውን ለህክምና ከማውጣት በተጨማሪ ሕይዎታቸውን ለማትረፍ የብድር እዳ ውስጥ እንደገቡ ነው የተናገሩት። ተመሥገን የምለው በሕይዎት መቆየታችንን ነው የሚሉት እናት የኑሮ ሁኔታቸው ተዛብቶ መቸገራቸውን ነግረውኛል። ምክንያቱ ምን ይሆን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ እናት ዓለምአንች ሲመልሱ በአካባቢያቸው ሰዎች በወባ በሽታ ቀድመው ሲታመሙ ነገ እኔም ነው ብሎ በማሰብ ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረግና ሲታመሙም ፈጥኖ አለመታከም እንደሆነ ገልጸውልኛል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የሚዲያ ተግባቦት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ወሳኝነት እንዳለው ባስተላለፉት መልእክት አስገንዝበዋል። በሰላም እጦት ምክንያት ክልሉ በተወሳሰብ የጤና ችግሮች ውስጥ መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመከላከልም የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል።
ባለፉት አራ
ት ወራት 1 ሚሊየን 20 ሺህ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው መታከማቸውን ገልጸዋል። በሽታው እንዲቀንስ፣ ኅብረተሰቡ በወቅቱ እንዲታከም የሚዲያው ተግባቦት በተለይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስታውእጾ ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
በቀጣይ የተወሳሰበውን የጤና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ተግባቦት አስፈላጊ በመሆኑ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) ተቋሙ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ 2 መቶ 22 ወረዳዎችን በመለየትም የወባ በሽታን ለመከላከል ሲሠራ ቆይቷል፤ ውጤትም ተገኝቷል ብለዋል። በቀጣይ በሽታውን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
በቀጣይ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው የበሽታዎችን ቀድሞ መቆጣጠርና መከላከል ተግባርን ስኬታማ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የመከላከልና የማከም የጤና ፖሊሲን በመተግበር የወባና ሌሎች በሽታዎች የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ችግሩን መቀነስ ተችሏል ብለዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራው ኀላፊነት ከፍተኛ ነው ብለዋል። በቅንጅት በሚዲያ ዘርፉ በተሠራው ሥራም ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።
የመረጃ ተደራሽነትን በማሳደግ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ በውጤታማነት ለመከላከል የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችንና የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ቀጣይ ሥራዎችንም ኀላፊነት ወስደው ማኅበረሰብ ተኮር የግንዛቤ ሥራዎችን እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!