“በቫይረሱ የሚያዙ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ በመኾኑ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይገባል”ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)

59

ደሴ: ኅዳር 22/2017ዓ.ም (አሚኮ) በሃገራችን ለ36ኛ ጊዜ ታስቦ የሚውለውን የዓለም ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ”ሰብዓዊ መብት ያከበረ የኤች አይቪ ኤድስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት እየተደረገ ነው። በውይይቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ፤ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በአደገኛ ኹኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በክልሉ ያለው የስርጭት ኹኔታም በወረርሽኝ ደረጃ ስለመኾኑ አመላክተዋል።

የስርጭት ምጣኔውን ለመቀነስ በየዘርፉ መረባረብ ይጠይቃል ያሉት አቶ አብዱልከሪም፤ እየታየ ያለውን መዘናጋት በመቀነስ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል። ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍም ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም ነው የገለጹት። በተለይም በወጣቶች እና በሴቶች ላይ በልዩ ትኩረት በመሥራት ቫይረሱ በአምራች ኀይሉ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ መግታት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኤችአይቪ ኤዲስ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት በመኾኑ፤ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መሥራት ይገባል ብለዋል። በተለይም በክልሉ በቫይረሱ የሚያዙ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ በመኾኑ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተደራጀ የጸጥታ መዋቅር መገንባት አስፈላጊ እንደኾነ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ገለጹ።
Next articleየመረጃ ተደራሽነትን በማሳደግ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ።