ሳምንቱ በታሪክ

48
ዳኛቸው ወርቁ!
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በልብ ወለድ ድርሰቱ ባነሳቸው ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ የከፍታ እርከን እንዳሸጋገረ ይነገርለታል ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፡፡ ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው የተወለደው በ1928 ዓ.ም ነው፡፡ ለዳኛቸው ታላቅነት እና የተስተካከለ ሕይወት አባቱ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
አባቱ አቶ ወርቁ በዛብህ ከጊዜው የቀደመ ተራማጅ ሰው እንደነበሩ አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
«እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ (1967 ዓ.ም.) ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲ እና ተርጓሚ እንደነበርም ይገለጻል።
በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ አዲስ ዘዴን የሞከረ እና ተወዳጅ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነበር። እንደሌሎቹ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች፣ ሥነ ጽሑፍ የነፍስ ጥሪው እና የተፈጥሮ ስጦታው ብቻ አልነበረም፡፡
ሥነ ጽሑፍን እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የተማረ፣ በዚህም በወቅቱ ከነበሩት ደራሲዎች በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ይለያልም ይሉታል፡፡
ዳኛቸው ወርቁ የጻፈው በአማርኛ ብቻ አልነበረም፤ በእንግሊዝኛ ሥራዎቹም ጭምር ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ በ1973 የታተመው ‘The Thirteenth Sun’ የተባለው መጽሐፉ ምዕራቡን ዓለም የማረከ ሥራው ነው፡፡ መጽሐፉ በፖርቱጋልኛ፣ በጀርመንኛ እና በቻይንኛ ተተረጎሞ በሰፊው ተነቦለታል፡፡
ዳኛቸው ወርቁ «አደፍርስ» 1962 ዓ.ም በተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ ባነሳቸው ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ ከፍታ ያሸጋገረ ድንቅ ደራሲም ነው፡፡ ታዋቂው ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ የነበረው ዳኛቸው ወርቁ ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም. ታሞ አረፈ። በተወለደበት ደብረ ሲና ከተማም ቀብሩ ተፈጸመ።
👉አለቃ ታዬ ገብረማርያም!
አለቃ ታዬ ገብረማርያም በዚህ ሳምንት ኅዳር 21/1853 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ ከምከም ቀሮዳ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ፡፡
አለቃ ታዬ ቦምቤ (ህንድ) ይኖሩ ወደ ነበሩት አጎታቸው ሂደው የውጭ ቋንቋዎችን እና ሰፋ ያለ የሃይማኖት ትምህርትን፣ የታሪክ እና የሰዋው መጽሐፍትን ከላቲን፣ ከግሪክ እና ከዓረብ ቋንቋ አጠኑ፡፡
በዚህ ዕውቀታቸው ወደ ትውልድ ቦታቸው ሄደው ዝነኛ ኾኑ፤ ይህም የወቅቱ የጎጃም እና በጌምድርን ያስተዳድሩ የነበሩት ቢትወደድ መንገሻ ሰምተው አስጠርተው ከታላላቅ ሰዎች ጋር ያስተዋውቋቸዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ አጼ ምኒሊክ ልከዋቸዋል፡፡ አለቃ ታዬ በ1891 ዓ.ም ወደ ሸዋ ሄደው ከአጼ ምኒሊክ እና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ደነባ ላይ ተገናኝተው ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተርጉመው እና አስፋፍተው የፃፉትን የሰዋሰው መጽሐፍ አበረከቱ፡፡
አጼ ምኒሊክም በሙያቸው ተደስተው እና ሸልመው ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዲያስተምሩ ላኳቸው፡፡
እስከ 1896 ዓ.ም መጨረሻ ጎንደር እያስተማሩ ተቀምጠው በዚሁ ዓመት የጀርመን ንጉስ ግዕዝ እና አማርኛ አጠናቆ የሚያውቅ የውጪ ቋንቋም የሚናገር ሰው ሲፈልጉ አጼ ምኒሊክም አለቃ ታዬን ላኩላቸው፡፡
አለቃ ታዬም በማስተማር እና በመመራመር ከአራት ዓመት በላይ አውሮፓ ቆዩ፡፡ አለቃ ታዬ በአውሮፓ በቆዩባቸው ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወስደው ጀርመን የሚገኙ 130 ቅርሶችን ዝርዝር ለአጼ ምኒሊክ በመላክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ብዙ ጉትጎታዎችን አድርገዋል፡፡
በ1912 ዓ.ም. በተቋቋመው ካቢኔ ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ ኾነው በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጲያ ሕዝብ ታሪክ የሚል መጽሐፍንም አሳትመዋል፡፡
የመመሠጋገን ቀን!
ልክ በዚህ ሳምንት ኅዳር 17 ቀን 1789 አሜሪካውያን የሚመሠጋገኑበት ቀን ያስፈልጋል በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ የምሥጋና ቀን የታወጀበት ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን አሜሪካውያን ላገኙት አገልግሎት እና እርስ በርሳቸው ያላቸውን ክብር እና አድናቆት ይገላለጹ ዘንድ ትልቅ ፍላጎት ነበራቸው፡፡
ይህም በአሜሪካውያን ዘንድ ያለውን መተሳሰብ ከፍ ያደርጋል ብለው ያሰቡት ፕሬዚዳንቱ ቀን ተቆርጦለት ይከበር ዘንድ መወሰን እናዳለበት እና ለዚህም ተግባራዊነት ያላሰለሰ ጥረት ስለማድረጋቸው ነው የሚነገረው፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚደንት ጆርጅ ዋሽንግተን ኅዳር 17 ቀን 1789 “የሕዝብ የምስጋና ቀን” የሚል አዋጅ ማውጣት ቻሉ፡፡ በአዲሱ ሕገ መንግሥታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ የምሥጋና ቀን ተከበረ።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች በጋራ ኮሚቴያቸው ሕዝቡ ሁሉ እንዲመሠጋገኑ እና ለተሰጣቸው ሁሉ አመሥጋኝ እንዲኾኑ ጠይቀዋል። እኔ ለዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ የምስጋና ቀንን እመክራለሁ ሲሉ ቀኑ ምን ያክል አስፈላጊ እና በዜጎች መካከል የሚፈጥረውን መልካም ወዳጅነት ስለመግለጻቸው ይነገራል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በኅብር ላይ የተመሰረተ አንድነት እና ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ይኖርብናል” አምባሳደር ተፈራ ደርበው
Next articleከ900 በላይ ወጣቶች የሰላም ዘብ ለመኾን ሠልጥነው ወደ ሥራ ገቡ።