
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን “ሥነ ምግባርን በማጎልበት እና ሙስናን በመከላከል ረገድ የምክር ቤቶች ሚና” በሚል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ከክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብሳቢዎች እና አማካሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ የሥነ ምግባር ግንባታን ማስፋፋት፣ በአሠራር ሥርዓት ላይ ጥናት ማድረግ፣ የሙስና ወንጀልን መከላከል፣ ሃብት መመዝገብ እና ማጣራት ዋና ዎቹ ናቸው።
በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሠጤ የሥነ ምግባር እና የሞራል እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ሙስናን ለመከላከል የተሠጠው ትኩረት ዝቅተኛ ከመኾኑ ጋር ተዳምሮ በተቋማት ውስጥ ሙስና እየተስፋፋ ይገኛል ብለዋል። በቅርቡ በድርጊቱ በተሳተፉ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ነው የገለጹት።
በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ተቋማት ተግባሩን በእቅድ ጭምር አካተትተው እንዲሠሩ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠሩም የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ለሙስና ተጋላጭ የኾኑ ተቋማት ለብልሹ አሠራር እና የሙስና ተጋላጭነት ምክንያቶችን በመለየት እንዲፈቱ እና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ ትኩረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ትኩረት አድርገው እንዲሠሩም ተጠይቋል። የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማት ግብረ ገብነት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!