
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ በዓደዋ መታሰቢያ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የበዓሉ ዓላማ ፓርቲው ከምሥረታው ጀምሮ እስካሁን ያደረገውን ጉዞ ለመዘከር እና ቃላችንን ለማደስ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ የትግላችን መዳረሻ ጠንካራ ሀገረ መንግስሥት መገንባት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ “ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው” ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የታሪክ እጥፋት የተመዘገበበት እንደ ነበርም አስታውሰዋል። በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት አቶ አደም በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ ውጤቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!