ብልጽግና ፓርቲ ሁለንተናዊ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሠራ ያለ ፓርቲ መኾኑ ተገለጸ፡፡

36

ደሴ: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ለሴቶች የፖለቲካ ውክልና ማን እንደ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ከቀበሌ እስከ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሴት መሪዎች የተሳተፉበት የሴቶችን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረቱን ያደረገ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ ሴት መሪዎች ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት ማምጣት ከተቻለ በርካታ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ሴቶችን ወደ መሪነት ማምጣት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አዝመራ ማስረሻ ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት አምስት ዓመታት ሴቶችን በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ በማድረግ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ከተማ በፖለቲካው ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ እየቀነሰ መጥሏል ያሉት ኀላፊዋ የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማ የሴቶችን አቅም በማጎልበት የተሻለ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ብልጽግና ፓርቲ ሁለንተናዊ የኾነ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሠራ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡

የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማረጋገጥ በሴት መሪዎች የሚመራ ፎረም ማዘጋጀት ለሚታዩ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ለማስቀመጥ እንደሚያስችልም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
Next article“ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው” አቶ አደም ፋራህ