
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
የመስኖ አምራች አልሚዎች በዓል በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ፣ በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት ተከብሯል። የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑ ተመላክቷል፡፡
መርጌታ አዱኛ መለሰ በመስኖ ሥራ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በማልማት ከ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የመስኖ ልማታቸውን ወደ 5 ሄክታር በማሳደግ የቸሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመስኖ ሥራ ጥረትን እንደሚጠየቅ የተናገሩት መሪጌታ አዱኛ ነገር ግን ክረምትን ጠብቀው ከሚያምርቱት ምርት የተሻለ ጥቅም እንደሚሰጥ ነው ያመላከቱት፡፡
ሌላኛው አልሚ አቶ አህመድ አሻግሬ በመስኖ ሥራው 4 ሄክታር መሬት እያለሙ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሚያለሙት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
አቶ ቢትወደድ ብርሃኑም በመስኖ ሥራ ሕይወታቸውን እንደቀየሩ ተናግረዋል፡፡ የመስኖ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የአፈር መዳበሪያ፣ የነዳጅ እና የውኃ መሳቢያ ጀኔሬተር ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡
የመስኖ አልሚ አርሶ አደሮች በዓል ዋና ዓላማው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጤናው ፈንታሁን ተናግረዋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር በዚህ ዓመት ከ200 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እንዳሰራጩም ገልጸዋል። በቂ የአፈር መዳበሪያ መኖሩን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ከሰው ሰራሽ መዳበሪያ ባሻገር አልሚዎች ኮምፖስት በማዘጋጀት የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት ይለማል ተብሎ ከታቀደው ከ2 ሺህ 600 ሄክታር መሬት 1 ሺህ 500 ሄክታሩ መልማቱንም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!