በዓሉ የጋራ እሴቶችን ለማድመቅ እና የጋራ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ መኾኑ ተጠቆመ።

30

ደሴ: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ሁነቶች በኮምቦልቻ ከተማ እየተከበረ ነው።

በዓሉ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል የተወከሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

የበዓሉ ተሳታፊ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዋ ሲስተር እስከዳር እሸቱ በዓሉ በዚህ ሁኔታ መከበሩ ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸውን በሚገባ እንዲያንፀባርቁ እና የእርስ በእርስ ትስስራቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ዕለቱ የብዝኀ ማንነት ባለቤት በኾነችው ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ መከበሩ የተለየ ትርጉም አለው ያሉት ሌላኛው ተሳታፊ አቶ መስፍን አበራ ልዩነቶችን በማከበር በመቻቻል መርህ ማስተናገድ እንደሚቻል በታዳጊዎች አዕምሮ ማስረጽ ይገባል ነው ያሉት።

በዕለቱ ደም ሲለግሱ አሚኮ ያገኛቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ሱሌይማን አህመድ እና ቃልኪዳን ድምጸ ሰብዓዊነትን ብቻ በማስቀደም በደም እጦት ምክንያት የምታልፍን ሕይዎት በመታደጋቸው የተለየ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሁሴን አሕመድ የቀኑ መከበር በሕዝቦች መካከል የጋራ እሴቶችን ለማድመቅ እና የጋራ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አብራርተዋል።

በዓሉ የተለያዩ እሴቶች፣ ባሕሎች እና ትውፊቶች ጎልተው እንዲወጡ ከማድረጉም ባሻገር ልዩነቶችን በውይይት እና በሃሳብ የበላይነት በመፍታት ሰላምን ለማጽናት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የፓናል ውይይት፣ የደም ልገሳ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ፣ የሰርከስ ትርዒት እና የተለያዩ ባሕላዊ ጭፈራዎች ቀርበዋል።

ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦቱን ተከትሎ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል ለማረም ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።
Next article“የመገጭ ፕሮጀክት ለውጥ ከተደረገበት በኃላ በጥሩ መንገድ እየተሠራ ነው” አብርሃም በላይ (ዶ.ር)