የሰላም እጦቱን ተከትሎ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል ለማረም ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።

32

ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን ተቋማዊ የቅንጅት አሠራር ለውጤታማ የፍትሕ አሥተዳዳር ያለውን አስተዋጽኦ በደሴ ከተማ እየገመገሙ ነው።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ከክልሉ የሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ወንጀል በየጊዜው እየረቀቀ እና አየተበራከተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፉ የተሠጠን ኀላፊነት በተገቢው አለመወጣት እየጎላ መምጣቱን ጠቁመው መድረኩ ሕዝብ ማገልገልን ታሳቢ አድርጎ እየገመገመ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

የ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመትን አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ውበቱ አለ ፍትሕን ለማረጋገጥ በርካታ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከቅንጅታዊ አሠራር ውስንነት የተነሳ በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡ ቅንጅት በሚጠይቁ ጉዳዮች ከመገፋፋት በመውጣት የድርሻን ማበርክት ይገባል ነው ያሉት።

ኀላፊው በቅንጅታዊ አሠራሩ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን በማድረግ ዘመናዊ የወንጀል መከላከል እና የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት፣ የተመዘበረን የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረት ማስመለስ ላይ ከወትሮው በላቀ ለመፈፀም ቅንጅታዊ አሠራሩ ሊኖር ይገባል ብለዋል። ቅንጅታዊ አሠራር የተቋም የመፈፀም አቅም የሚያጎለብት እንደኾነም አመላክተዋል።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ለፍትሕ እና ፖሊስ ተቋማት ፈታኝ ቢኾንም ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

በዚህ ወቅት ሕግን ለማስከበር አየተሠራ ያለው ሥራ ጥሩ ቢኾኑም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ መውስድ ይገባል ብለዋል።

ከሙስና ጋር በተያያዘ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሥራት የሚጠይቅ እንጂ መደበቂያ እየፈለጉ ማድበስበስ አያስፈልግም ብለዋል። ከዚህም መውጣት ካልተቻለ ከችግሩ መሻገር እንደማይቻልም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አሁናዊ ሁኔታው እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አለመቻል እና መሥራት ሲጀመርም የማያሠራ ኀይል መኖሩ ፈታኝ ሁኗል ነው ያሉት።

ተቋማት ለችግሩ በቂ ምላሽ ለመስጠት በብቃት፣ በቅንጅት እና በሚስጥር ጠባቂነት መረጃ መሠብሠብ፣ መመርመር እና አጠናክሮ ማቅረብ እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት።

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ዘርፍ ኀላፊ አያሌው አባተ ( ዶ.ር) የፖሊስ እና ዐቃቢ ሕግ ቅንጅታዊ አሠራርን ለውጤታማነት በማጠናከር በሁለቱ ተቋማት እና በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር እየገጠሙ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚቻልበትን አቅጣጫ አመላከተዋል።

የወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ለሕዝብ እና መንግሥታዊ ሥርዓት መፅናት ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ዶክተር አያሌው የሁለቱ ተቋማት ትብብር እና ቅንጅታዊ አሠራር ትኩረት የሚያስፈልገው መኾኑን በገለጻቸው አሳይተዋል።

ከዚህ በፊት ቅንጅታዊ አሠራር የነበረ ቢኾንም ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የወንጀል ጉዳዮችን በመለየት እና አሠራር በመዘርጋት ሂደት ውስንነት መኖሩን አመላክተዋል።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን በምሳሌነት አንስተው ወንጀሉ አሰቃቂ እና ሕጻናትም ሳይቀሩ ለከፍተኛ አደጋ የሚጋለጡበት ብሎም የተደራጁ ወንጀለኞች የሚሳተፉበት በመኾኑ በልዩ ሁኔታ ተቋማዊ አደረጃጀት እና ቅንጅት ተፈጥሮ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል።

በቢሮ ደረጃ ብዙ ችግሮችን የሚፈታ የአደረጃጀት ጥናት መጀመሩን፣ ከፍርድ በመለስ ጉዳዮች በፍትሕ ቢሮው የሚቋጩበት የአሠራር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ መዘጋጀቱን፣ ከዲጂታላይዜሽን አኳያ ብዙ ጅምር እና የተጠናቀቁ ሥራዎች መኖራቸውን እና ይህም ቅንጅታዊ አሠራርን ለማምጣት አስተዋጽኦው እንዳለው አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ጎጃም ዞን 19 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል።
Next articleበዓሉ የጋራ እሴቶችን ለማድመቅ እና የጋራ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ መኾኑ ተጠቆመ።