
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ንቅናቄን በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በሰባታሚት ቀበሌ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም አርሶ አደሮች በተገኙበት አስጀምሯል።
አርሶ አደር ላቀው አያሌው እና አንማው ሙጬ በትራክተር በማሳረስ የሚጠቀሙትን አርሶ አደሮች ሲያዩ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ እነሱም በትራክተር በማሳረስ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በበሬ እያረሱ ጊዜ እና ጉልበታቸውን ከማባከን ለመዳን እና የበለጠ ምርት ለማምረት መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ዞኑ ታላላቅ ወንዞች፣ ሰፊና ምቹ መሬት እንዲሁም እንደ ቆጋ ያሉ የመስኖ ልማት ቦታዎች ያሉት በመኾኑ ለበጋ መስኖ ልማት ምቹ ነው ብለዋል። የአርሶ አደሮችን ተነሳሽነትንም ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ በዞኑ 24 ሺህ 269 ሄክታር መሬት በመስኖ ይለማል፤ ከዚህ ውስጥም 19 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩ 8 ትራክተሮች በተጨማሪ 13 ትራክተሮችን በ82 ሚሊየን ብር ለእያንዳንዱ ወረዳ ሁለት ሁለት ትራክተር ተከፋፍሏል ብለዋል።
በዚህ ዓመት 780 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል፤ ለዚህም 58 ግድቦችና የወንዝ ጠለፋ፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር አቅርቦት እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችም አድርገናል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!