
ባሕር ዳር: 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በጤናው ዘርፍ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይል ከማሟላት ባለፈ አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙ ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ እያከናወነ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ተናግረዋል። አሁን ላይ በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከሚፈለገው የሰው ኀይል ውስጥ 55 በመቶው ብቻ መሟላቱንም ገልጸዋል። የባለሙያ እጥረት ችግሩ በጤና ጣቢያዎች የጎላ ነው ተብሏል።
ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በዚህ ዓመት የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሰው ኀይል ማሟላት ትኩረት ላይ ተደርጓል። ከዚህ ባለፈ በተቋማት የሚገኙ ሠራተኞችን ውጤታማነት መመዘን የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በቢሮው ብቻ ይሠራ የነበረውን ዝውውር ወረዳዎች እና ዞኖች በራሳቸው ዝውውር እንዲፈጽሙ ተደርጓል።
የሙያተኞች የደረጃ ማሳደግ ሌላው ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ ነው። በዚህ ዓመት 4 ሺህ የሚኾኑ ባለሙያዎች በተለያየ የሙያ እና የትምህርት ደረጃ ለማስተማር መታቀዱን ለአብነት አንስተዋል። በክልሉ በሚገኙ 34 ቦታዎችም ለባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ እድገት ማጎልበቻ ሥርዓት በመዘርጋት የሙያ ብቃት ማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። 750 የሚኾኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት የማረጋገጥ ሥራም መሠራቱን ነው የገለጹት።
ቢሮው አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ እየሠራ ቢኾንም አሁንም በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት 141 ጤና ኬላዎች እና 12 ጤና ጣብያዎች ከአገልግሎት ውጭ መኾናቸውን ነው የገለጹት። በዚህም ጤና ኬላዎች እስከ 3 የሚደርሱ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ በጤና ጣብያዎች ደግሞ እስከ 60 የሚደርሱ ባለሙያዎች ሥራ አቁመዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በማኅበረሰቡ አገልግሎት መሥጠት ባለመቻሉ ታካሚዎች ለጉዳት መጋለጣቸውን ነው የገለጹት።
የጤና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሠጡ ማንኛውም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!