
ሰቆጣ: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእኩልነት እና የአንድነት ቀን የኾነው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ትናንት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የተገኙት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ አንድነትን እና ውበትን በሚያሳይ መልኩ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
የአንድነታችን ማሳያ፣ የተግባቦታችን ምልክት፣ የኢትዮጵያዊነት አርማ የኾነው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ስናከብር ዘር፣ ቋንቋ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ውበት እንጅ የልዩነት ምክንያት አለመኾኑን እያሰብን ሊኾን ይገባል ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር እንጅ እርስ በእርስ የሚያጠላልፈን ሊኾን አይገባም ነው ያሉት አቶ ኃይሉ።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ የዋግ ሕዝብ ባሕሉን እና ወጉን ለዓለም እንዲያሳይ በር የከፈተ በዓል መኾኑን በዕለቱ ታዳሚ የነበሩት አቶ ፍቅሬ ደረጀ ተናግረዋል። ከጋዝጊብላ ወረዳ የመጡት የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ማርታ ደባሽ በየዓመቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ እና ውበት ለዓለም የምታሳይበት በዓል ነው በማለት ገልጸውታል።
ብዙ ስንኾን እንደ አንድ፤ አንድ ስንኾን ብዙ መኾናችንን በቋንቋችን፣ በባሕላችን እና በአለባበሳችን ደምቀን የምንታይበት ነው ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር አንዱ የአንዱን ባሕል እና ቋንቋ ሊያከብር ይገባል ያሉት ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አድና ምህረቱ ናቸው።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለሁሉም ብሔረሰቦች ማንነታቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እድል የፈጠረ ነው የሚሉት ወይዘሮ አድና ይህንን እድል በመጠቀም እኛም ከገባንበት የሰላም እጦት ለመውጣት የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ቀንን እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀመው ይገባል ነው ያሉት።
በዓሉን በማስመልከትም የፓናል ውይይት ተደርጓል። በተጓዳኝም ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በማስመልከት ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትም ተሰጥቷል።
በበዓሉ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከወረዳዎች የመጡ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!