ኢትዮጵያ ባለፉት 6 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቧን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

70

አዲስ አበባ: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ መካሄዱ ይታወሳል። ይህንን ጉባኤ አስመልክቶ የኘላንና ልማት ሚኒስቴር ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠዋል።

መግለጫውን የሰጡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ጉባኤው የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር ብሎም ዘላቂነት ያለው የአየር ንብረት ለውጥን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንደነበር አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራት በጉባኤው መነሳቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ዘላቂ የኾነ የአየር ንብረትን ለማስጠበቅ ትልቅ ሚና እንዳለው በጉባኤው መነሳቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ተግባራዊ በማድረግ እስካሁን 40 ቢሊዮን ችግኝ መትከል መቻሏን አንስተዋል። በግብርናው ዘርፍም ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ተግታ እየሠራች መኾኑን ጠቅሰዋል። ለአብነትም በስንዴ ልማት ብቻ በመደበኛው እና በበጋ መስኖ 23 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ማምረቷን ተናግረዋል።

በሌማት ቱሩፋትም እንደ ሀገር ያስመዘገበችውን ተጨባጭ ለውጥ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ተችሏል ብለዋል። የታዳሽ ኀይል አቅርቦት ላይም ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑን በጉባኤው ተነስቷል ብለዋል። ለአብነትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመገንባት አፍሪካን በኀይል አቅርቦት ለማስተሳሰር አልማ እየሠራች መኾኑን በጉባዔው ማንሳት ተችሏል ነው ያሉት።

እስካሁንም ጅቡቲን፣ ሱዳንን እና ኬኒያን ከኢትዮጵያ ጋር በኀይል ማስተሳሰር መቻሉን አንስተዋል። በኢኮቱሪዝም፣ በትራንስፖርት እና በከተማ አረንጓዴ ልማት ዘርፎችም ሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሏን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ መቻሉን ነው ሚኒስቴር ዴኤታው የገለጹት።
ሌሎች ሀገራትም ከኢትዮጵያ ልምድና ተሞክሮ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

በአየር ንብረትን ለውጥን ተጋላጭ ለኾኑ እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የ300 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግ በጉባኤው መወሰኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነችው ያለውን ተጨባጭ ለውጥ የተለያዩ ሀገራት በፋይናንስ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ከሀገራት ጋር በጋራ እና በትብብር ለመሥራት የሁለትዮሽ ሥምምነቶችና ውይይቶች በተናጠል ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ 2027 ዓ.ም የኮፕ ጉባዔን እንድምታዘጋጅም ተጠቁሟል። ከኅዳር 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ጉባኤ ላይ ከ198 አባል ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ተሳትፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመጤ አሉታዊ ባሕል እና አደንዛዥ ዕፅ በከፍተኛ ኹኔታ ተስፋፍቷል።
Next article“የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እንድናጠናክርበት ሕገ መንግሥቱ ያደለን ልዩ ቀን ነው” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር