
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እየተስፋፋ ያለውን መጤ አሉታዊ ባሕሎችን እና እና አደንዛዥ ዕፅ ለመግታት የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተገልጿል። የአማራ ክልል የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የወጣቶችን ጉዳይ አካቶ ትግበራ እና አሉታዊ መጤ ባሕል፣ አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ግብረ ኃይል የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ ባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሠ በክልሉ መጤ አሉታዊ ባሕል እና አደንዛዥ ዕፅ በከፍተኛ ኹኔታ መስፋፋቱን ተናግረዋል። አሁን ላይ ለተከሰተው ቀውስ አባባሽ ምክንያትም ኾኗል ነው ያሉት። ከችግሩ ለመውጣት ሁሉም በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ ወጣቶች በመጤ ባሕል እና አደንዛዥ ዕፅ እየወደቁ መኾናቸውን ተናግረዋል። እያንዳንዱ ተቋም ወጣቶችን ማዕከል አድርጎ እየሠራ መኾኑን ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባ አመላክተዋል። እንደ ክልል የገጠመው የሰላም እጦት ወጣቶችን ሥራ አጥ የሚያደርግ መኾኑን የተናገሩት ኃላፊው ሥራ አጥነት ወጣቶችን ወደ አሉታዊ እና መጤ ባሕሎች እንዲገቡ ይገፋፋቸዋል ነው ያሉት።
ሁሉም ተቋማት የወጣቶችን ጉዳይ በአካቶ ትግበራ መርሕ በመሥራት የወጣቶችን ሕይዎት መታደግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!