“በበጋ ስንዴ ልማት በመትጋት ከራስ አልፎ ምርትን ወደ ውጭ መላክ መቻል የሉዓላዊነት እና የሀገርን ክብር የማስመለስ ጉዳይ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

59

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ትራክተሮችን ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች አስረክቧል። በዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሰባታሚት ቀበሌ አንበሸን ጉድኝት ላይ በ78 ሄክታር መሬት ላይ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሣህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እና ሌሎችም የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የመስኖ ሥራ የተጀመረበት የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሰባታሚት ቀበሌ የሰላም ችግር እንደነበረት አስታውሰዋል። በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱንና የበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት ለአርሶ አደሮች ትራክተር ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። በአርሶ አደሮች ተነሳሽነት እና በመንግሥት ድጋፍ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። እየተሠራ ያለው ሥራ በበጋ መስኖ ስንዴን ማልማት እየተለመደ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል። ከመንግሥት የሚጠበቀው ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ትራክተር ማቅረብ ነው፤ ይህንንም ባለፉት ሁለት ዓመታት እየሠራነው ነው ብለዋል። ትራክተሮችንም በአነስተኛ ዋጋ ለአርሶ አደሮች ማቅረብ ችለናል ነው ያሉት።

”ስንዴን በበጋ መስኖ የማምረት ልምድ የማይቀለበስ የግብርና አማራጭ ኾኗል” ሲሉም ተናግረዋል። ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይም ዋነኛ አጀንዳችን ኾኗል ነው ያሉት። በተሠራው ሥራ እንደ ሀገር በምግብ ራሳችን በመቻል ከውጪ ማስገባትን አቁመናል ብለዋል። በውስን መልኩ ወደ ውጪ መላክ ተጀምሯልም ብለዋል። “በበጋ ስንዴ ልማት በመትጋት ከራስ አልፎ ምርትን ወደ ውጭ መላክ መቻል የሉዓላዊነት እና የሀገርን ክብር የማስመለስ ጉዳይ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው ጥረትም በዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ፋኦ ጭምር እውቅና የተሰጠው ነው ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አቶ መሐመድ እድሪስን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር በማድረግ ሾሙ።
Next article19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአፋር ክልል ደረጃ በሰመራ ከተማ እየተከበረ ነው።