
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታች እና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ይገኛል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ቀኑን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢሮ ኀላፊዋ ቀኑን ስናከብር አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን መብት እና ተጠቃሚነት እያሰብን ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። ከዚህ ቀደም በችግር ውስጥ ላሉ አካል ጉዳተኞች የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የመሥሪያ ቦታ ድጋፎች መደረጋቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል። የአካል ጉዳተኞን ሕይወት በዘላቂነት በማሻሻል በኩል አኹንም ሰፊ ሥራዎች እንደሚጠበቁም ገልጸዋል።
ከአመለካከት አንጻር በራሳቸው በአካል ጉዳተኞችም ኾነ በማኅበረሰቡ ዘንድ መስተካከል ያለባቸው እሳቤዎች ስለመኖራቸውም ወይዘሮ ብርቱካን ጠቁመዋል። “አካል ጉዳተኞች ዕድሉን ካገኙ እንደማንኛውም ሰው ይችላሉ” ነው ያሉት። አካባቢያዊ ችግሮች ለአካል ጉዳተኞች ፈተና እየኾኑባቸው ነውም ተብሏል በመግለጫው። መንገድ፣ ሕንጻዎች እና መሰል መሠረተ ልማቶች ሲገነቡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መኾን እንዳለባቸውም ቢሮ ኀላፊዋ አሳስበዋል።
በሁሉም ዘርፍ አካታች እና ሁሉን ዓቀፍ ድጋፎች ለአካል ጉዳተኞች ማረጋገጥ፣ የመሪነት ሚናቸውን ማሳደግ እና ጠንካራ አደረጃጀቶች እንዲኖራቸው መሥራት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ናቸውም ብለዋል።
ሁሉም አካል ለአካል ጉዳተኞች ዘላቂ ሕይወት መሻሻል እና ለተጠቃሚነታቸው የየራሱን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!