የሳይበር ሉዓላዊነት

25

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ሉዓላዊነት ሲነሳ መልከዓ ምድራዊ ሉዓላዊነት ብቻ ይምሰል እንጅ ዘርፈ ብዙ እንደኾ በኢንፎርሜሽን ደኅንነት አገልግሎት የኢንፎርሜሽን ኢንሹራንስ ዘርፍ አሥተባባሪ የኾኑት ሃኒቫል ለማ ይገልጻሉ፡፡ የሳይበሩ ዓለም ቀደም ተብሎ የሚታሰበውን የሉዓላዊነት ኹኔታ እንደቀየረው አሥተባባሪው ይናገራሉ፡፡

ይህም የቃሉን መገለጫ ስለመቀየሩ ነው የነገሩን፡፡ ከዚህ በፊት በምናውቀው የሉዓላዊነት ጽንሰ ሃሳብ መልከዓ ምድራዊ ድንበርን ብቻ ነበር የምናውቀው የሳይበሩ ዓለም ላይ ግን የሉዓላዊነት ጉዳይ ድንበር የለሽ ነው ይላሉ፡፡ የሳይበር ሉዓላዊነት እስከ ግለሰብ ድረስ የሚወርድ በመኾኑ የግለሰቦችም የሳይቨር ደኅንነት መጠበቅ እንደሚኖርበት ነግረውናል፡፡

የአንድ ግለሰብ የሳይበር ምህዳር መጠበቅ በዙሪያው ያሉትን ቤተሰቦቹን፣ ማኅበረሰቡን ክፍ ሲልም ከሀገር ጥቅም ጋር የሚያያዝ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ በግለሰብ ደረጃ ያለን የሳይበሩ ሉዓላዊነት መጠበቅ ሀገርን መጠበቅ እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት፡፡ በሀገር ደረጃ የሳይበር ሉዓላዊነትን መጠበቅ ሲባል የምንጠቀምባቸው ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ ይኾናል ነው ያሉት፡፡

እነዚህን መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ ደግሞ ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ የሚደርስ ጥቅም እንደሚኖረው ያስረዳሉ፡፡ ይህም ከሀገራዊ ሉዓላዊነት ጋር እንደሚገናኝ ነው ያብራሩት፡፡ የሳይበር ጥቃት ሲባል በየቀኑ በተሳሳቱ መረጃዎች እና መረጃ በማዛባት በግብይት ወቅት የሚጠቃውን ሰው ጨምሮ በሀገር ደረጃም አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን እንዳይሠሩ ማድረግን፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች በአግባቡ እንዳይሠሩ ማድረግ፣ መንግሥት ለዜጎች ሊሰጠው የሚገባውን አገልግሎት እንዳያደርስ ማስተጓጎል እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

በሰፊው ስንመለከተው እነዚህን መጠበቅ አስፈላጊ እንደኾነ እና ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር የሚገናኝ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህን መሠረት አድርጋ ከግለሰብ ጀምሮ የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ የጥቃት ሙከራዎችን ለመከላከል ጠንክራ እየሠራች እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡ የሀገርን የሳይበር መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ተጠየቀ።
Next articleበታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ561 ቶን በላይ ዓሣ ተመርቷል።