
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ከአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አድርጓል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት ከምክር ቤቶች ተግባር እና ኀላፊነት ውስጥ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ አንዱ ነው።
ሰብዓዊ መብት ሰው በመኾን የሚገኝ መብት መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ አሁን በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይከሰት ክትትል እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ትኩረት ተደርጓል ብለዋልአፈ ጉባኤዋ። የምክር ቤት አባላት ክልሉ ካለበት ችግር እንዲወጣ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በክልሉ በተፈጠረው ችግር በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥሰት እንዳይከሰት የሚያደርገው ክትትልም ለምክር ቤት አባላት አቅም የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ ፌቶል ሲያንኮር እንዳሉት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሰብዓዊ መብቶችን ማጎልበት እና ጥበቃ ማድረግ አንዱ ነው።
ችግሮችን በውይይት በመፍታት በግጭቱ ሊደርስ የሚችለውን የመብት ጥሰት ማስቆም ይገባል ብለዋል። በተለይም ደግሞ ተጋላጭ የኅብረተረብ ክፍሎችን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ምክር ቤቶችም ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ የመጠበቅ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ምክር ቤቶች ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብሩ ሕጎች መውጣታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ ያደርጋሉ። አሁን ላይ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍትሕ ተቋማት ጋር እየተሠራ መኾኑንም ዶክተር ደሴ ጥላሁን ገልጸዋል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲኾኑ ይደረጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!