ሰሞኑን በርካቶችን ያስቸገረው ጉንፋን መሰል በሽታ!

82

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳርን ጨምሮ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ጉንፋን መሰል በሽታ እየተከሰተ ነው፡፡ በዚህ ጉንፋን መሰል በሽታ በርካቶች ሲቸገሩ ተመልክተናል፡፡

👉 ለመኾኑ ይህ ጉንፋን መሠል በሽታ ምን ይኾን?

ጉንፋን መሰል የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች አመጣጣቸው በቫይረስ እንደኾነ የሚናገሩት በጋንቢ ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፒሻሊስት ዶክተር ኃይለማርያም አደራ ዓይነታቸው ብዙ እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡

👉መተላለፊያ መንገዳቸው፡-

የአብዛኞቹ የጉንፋን በሽታዎች መተላለፊያ መንገዳቸው ተመሳሳይ እንደኾነ የሚናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም በትንፋሽ፣ በንክኪ፣ በማስነጥስ ቀጥታ ከታካሚው  ወደ ጤነኛው ሰው ሊተላለፍ እንደሚችልም ነው ያስረዱት፡፡

በንክኪ ሲባል ሰላም በመባባል በሚፈጠር የእጅ ንክኪ፣ የበር ቁልፍ እና የበር መሳቢያዎችን፣ ጠረጴዛዎችን ሕመሙ ያለበት ሰው የሚነካ ከኾነ ጤነኛው ሰው እነዚህን የሚነካ ከኾነ በሚገባ እጁን ካላጸዳ በሽታው ሊተላለፍ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ነው የሚገልጹት፡፡ የበለጠ ጥናት የሚጠይቅ ቢኾንም ኮሮና መሰል የጉንፋን በሽታ እንደሚስተዋል ነው ያስረዱት፡፡

👉 መከላከያ መንገዶቹ፡-

የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ በሽታውን ለመከላከል ሁነኛ መንገድ ነው ያሉት ዶክተር ኃይለማርያም እጅን በሳሙና እና በውኃ በየጊዜው መታጠብ በተለይም እጅ ማንኛውንም ነገር ከነካ በኃላ በሚገባ ንጽሕናው እንዲጠበቅ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

እጅ ብዙ ጊዜ አፍ እና አፍንጫን እንዳይነካ ጥንቃቄ ማድረግ ሌላው መፍትሄ እንደኾነም  ነው ያስረዱት፡፡ ምንም እንኳን እጅ ወደ አፍ እና አፍንጫ እንዳይሄድ ለማድረግ አስቸጋሪ ቢኾንም በልምምድ ብዙ ጊዜ እጅ አፍን እና አፍንጫን እንዳይነካ ማድረግ እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

ብዙ ጊዜ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከጤነኞች ጋር ሲውሉ እና አብረው ሢሠሩ እንደሚታዩ የሚናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም በሽታውን ለመከላከል በበሽታው የተያዙ ሰዎች እረፍት እንዲያገኙ ቢደረግ በሽታውን ለመከላከል እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት፡፡

በቤት ውስጥ የሚደረገው ለሕሙማን እንክብካቤ እንዳለ ኾኖ አንዳንድ ጊዜ ሕመሙ ከበድ ብሎ ሌሎች ከበድ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያመጣ ስለሚችል ወደ ሕክምና ጣቢያዎች በማቅናት አስፈላጊውን ሕክምና ማግኘት እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡

👉ለምን ብዙ ሰዎች በዚህ ወቅት በጉንፋን መሰል በሽታ ይጠቃሉ?

ዶክተር ኃይለማርያም እንደነገሩን አሁን ላይ ብዙ ሰዎች የሚጠቁበት ምክንያት ወቅቱ በተለይም ለበሽታው አምጭ የኾኑ ቫይረሶች የሚመቻቸው ጊዜ እንዳለ እና በዛም ምክንያት ብዙ ሰው በበሽታው የመጠቃት እድሉ ከፍ ሊል እንደሚችል ነው የሚገልጹት፡፡ 

የሰዎች የአኗኗር ሁኔታ እና የጥንቃቄ ጉለት በሽታው በስፋት አብዛኛውን ሰው እንዲያጠቃ ምክንያት እንደሚኾንም ነው የጠቆሙት፡፡ በተለይ አሁን ላይ ትምህርት ቤት በመከፈቱ ትምህርት ቤቶች ላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ልጆች በመኾናቸው የጥንቃቄ ጉድለት ስለሚኖር በሽታው ብዛት ያላቸውን ሰዎች የማጥቃት እድሉን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡

ዶክተር ኃይለማርያም ለማሳያነት ትምህርት ቤት ይጠቀስ እንጅ ሰዎች በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጥንቃቄ ከሌለ በቀላሉ ብዙዎችን በሽታው ሊያጠቃ እንደሚችልም ነው የነገሩን፡፡

👉ጉንፋን የሚበረታባቸው ሰዎች ምን አይነት ሰዎች ናቸው?

ጉንፋን የሚበረታባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሳንባ፣ የአስም፣ የቲቪ በሽታ ኑሮባቸው ሳንባቸው ላይ ጠባሳ ያለባቸው እና የስኳር በሽተኞች ሲኾኑ በቀላሉ ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል የተናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ ከኾነ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ሊል እንደሚችል አረጋግጠዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ሰዎች የማይረዱት ሰዎች ሲጨነቁ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለሚዳከም ለጉንፋን በሽታ ተሎ እንዲጠቁ ሊያደርግ እንደሚችልም ነው ያብራሩት።

👉 ጉንፋን መሰል በሽታ እና የቤት ውስጥ ሕክምና፡-

አሁን ላይ በብዛት እየተስተዋለ ያለው ጉንፋን መሰል በሽታ በቤት ውስጥ የሚታከም እንደኾነ የተናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም ከፍተኛ የኾነ ሙቀት፣ የመገጣጠሚያ አካባቢ መቆረጣጠም በሕሙማኑ ላይ የሚኖር ከኾነ ማስታገሻ የሚኾኑ መድኃኒቶችን መውሰድ እንደሚቻል አስታውሰዋል፡፡ በተጨማሪም በቂ እረፍት ማድረግ፣ ፈሳሽ ነገር በደንብ መውሰድ፣ ሌላው አስፈላጊው ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ጉንፋኑ ደረጃው ከፍ ብሎ ወደማያቋርጥ ሳል፣ ከፍተኛ ሙቀት መኖር፣ ምግብ አለመውሰድ እና ትውኪያ ሲኖር ወደ ህክምና ተቋማት መምጣት ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ካሉ ከፍ ላለ ጉዳት ሊያጋልጡ ስለሚችሉ መታየቱ እንደሚመከር ነው ያሳሰቡት፡፡

👉ጉንፋን መሰል በሽታ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ በምን ይታከማል?

ጉንፋን መሰል በሽታዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ወደ ሕክምና ጣቢያ በሚመጡበት ጊዜ የራሱ ሕክምና እንዳለው የተናገሩት ዶክተር ኃይለማርያም ይህም በሦስት ደረጃ እንደሚታይ ነው ያብራሩት፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከጉንፋን ጋር ተደርቦ ሌላም በሽታ ሊኖር ስለሚችል አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ አንደኛ ደረጃ ጉንፋን ከኾነ ምክር ሰጥቶ በቤት ውስጥ እንዲታከም እና እንክብካቤ እንዲደረግለት እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡

ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ የደረሰ ከኾነ ግን ለመተንፈስም ስለሚቸገሩ የማሽን እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረው ለዚህም አስፈላጊው ሕክምና እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡ እንደታካሚው የዕድሜ ደረጃ እና የሕመም ሁኔታ አንቲ ባይዎቲክ መድኃኒት እንደሚታዘዝም ነው ያስረዱት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላሙ ባለቤት ኅብረተሰቡ ነው”
Next articleሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ተጠየቀ።