“የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላሙ ባለቤት ኅብረተሰቡ ነው”

37

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል። በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ካሳሁን ንጉሴ፣ የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ እንዲሁም ሌሎች የዞን እና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ካሳሁን ንጉሴ እንዳሉት የመድረኩ ዓላማ የተዛነፉ አመለካከቶችን በማረም ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ያለመ ነው። የመድረኩ ተሳታፊዎች በወረዳው ያለውን የሰላም ሁኔታ በመገንዘብና የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የምንፈልገውን ልማት ለማሳካት ሰላም ወሳኝ ነው፤ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላሙ ባለቤት ሕብረተሰቡ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ ሰላም የተረጋገጠበት አካባቢ ለመፍጠር ፅንፈኛ ኀይሎችን በቁርጠኝነትና በጀግንነት መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ወረዳው ተደጋጋሚ ፈተናዎች ገጥመውት የቆየ ቢሆንም በፈተናም ውስጥ ሆኖ ለውጦችን እያስመዘገበ መምጣቱን አስታውሰዋል። የዚህ የሰላም መድረክ ተሳታፊዎች ስለሠላም ምንነትና አስፈላጊነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባም ገልጸዋል። ከዚህ መድረክ በኋላም የሰላም አምባሳደር ሆነው በየአካባቢያቸው ካሉ የመንግስትና የፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ አሁን ያለውን ሰላም ማፅናት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት አቅዶ እየሠራ ነው።
Next articleሰሞኑን በርካቶችን ያስቸገረው ጉንፋን መሰል በሽታ!