የደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት አቅዶ እየሠራ ነው።

41

ደሴ: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በመቅደላ እና በተንታ ወረዳዎች በይፋ አስጀምሯል። አሚኮ ያነጋገራቸው የተንታና የመቅደላ ወረዳ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነታቸውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከአምናው የተሻለ ምርት ለማምረት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶች ከመንግሥት በኩል እንደደረሳቸው ጠቅሰው ምርጥ ዘር ግን በራሳቸው መሸፈናቸውን አንስተዋል። የመቅደላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰይድ አደም በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ 1ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በማልማት ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የተንታ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ አለባቸው በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በወረዳው በ 890 ሄክታር መሬት ላይ 30 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዘንድሮው የበጋ ወቅት 36 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ 21 ሺህ ሄክታር መሬቱ በበጋ መስኖ የሚለማ መኾኑንም ጠቁመዋል። ለዚህም እንዲያግዝ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ለአርሶ አደሩ መድረሱን ገልጸው፣ አዲስ የእርሻ ትራክተር እና የውሃ መሳቢያ ሞተር መሠራጨቱን ተናግረዋል። በክልሉ የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኤክስቴንሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቀኝአዝማች መስፍን በዘንድሮው ዓመት ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleላሊበላ ወደ ቀደመ ማንነቷ እንድትመለስ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።
Next article“የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላሙ ባለቤት ኅብረተሰቡ ነው”