“ገዥ ትርክትን በማስረጽ፣ በትጋት እና በቁርጠኝነት ይሠራል” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

80

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ክልላዊ የብልጽግና ፓርቲ የምሥረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት እና የፓርቲው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁ ፍቅሩ (ዶ.ር) ፓርቲው በአምስት ዓመታት ጉዞው በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል። በሕዝብ ግፊት እና በፓርቲ ሳቢነት የመጣው ሀገራዊ ለውጥ ቃልን በተግባር እየገለጠ፣ የለውጡን ፈተናዎች በጽናት እየታገለ፣ ጽንፈኞችን ከእነ ሃሳባቸው እያኮሰመነ፣ የሀገሪቱን ሥብራቶች በአስተማማኝ ኹኔታ እየጠገነ መምጣቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ በማቅናት ላይ የሚገኘው የለውጥ ዘመን መሪ ፓርቲ የኾነው ብልጽግና አምስት የስኬት ዓመታት በታላቅ ድል ማለፍ ችሏል ነው ያሉት። ብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት ነባር ሀገራዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶችን ማጎልበት መቻሉን ነው የተናገሩት። ባለፉት ዓመታት የሃሳብ ልዕልና በከፍተኛ ኹኔታ ዋጋ ያገኘበት፣ ሃሳቦች በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረቱበት እና የሕዝብን ፍላጎት የለዩ መኾናቸውን ነው ያስረዱት። ባለፉት ዓመታት የሚጨበጡ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ስለመመዝገቡም ነው ያስገነዘቡት።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚሠራው ዘርፈ ብዙ ሥራ ነባር ሀገራዊ አቅሞችን ለይቶ መጠቀሙን ተናግረዋል። ሀገራዊ ጥረቶችን አውቆ በመምራት የኢትዮጵያን ከፍታ የሚገልጡ ሥራዎችን ሠርቷል ነው ያሉት። በፈተናዎች አለመቆምን የሚያስተምሩ እምርታዊ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራት በከፍተኛ ቁርጠኝነት መከናወኑንም ነው የተናገሩት።

ስኬቶችን ለመግታት፣ የለውጥ ጥረቶችን ፍጥነት ለመቀነስ እና ሀገር ከቀውስ አዙሪት እንዳትወጣ ሌት ተቀን የሚሠሩ ከውጭ እና ከውስጥ እየተናበቡ ጠላቶች እንደነበሩም ገልጸዋል። የታሪክ ተወቃሾች መልከ ብዙ ጥፋቶችን በሀገሪቱ እና በክልሉ ሲያደርሱ ቆይተዋል ነው ያሉት። ክልሉ እነዚህ ኀይሎች በፈጠሩት ቀውስ ሰላሙ ተናግቶ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የጽንፈኛ ኀይሎችን እኩይ ዓላማ በአስተማማኝነት በመቀልበስ ዘላቂ ሰላምን በመትከል ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል። መጭውን ዘመን የሚዋጅ ምግባር በመላበስ፣ ተቋማዊ አቅም የመፍጠር ብቃትን በማሳደግ፣ የፓርቲውን እሳቤዎች እና አቋሞች በማስረዳት እና በመተግበር፣ ጠንካራ የሃሳብ እና የተግባር አንድነት የመፍጠር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

ሀገር እና ሕዝብን በታማኝነት በማገልገል፣ ምስጉን፣ ሕዝብ አገልጋይ ኀይሎችን የማስፋት እና የማብዛት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በትልቅ ልዕልና ከሕዝብ ፊት መቆም የሚያስችል አቅምን ከፍ በማድረግ ሕልምን እያጋሩ፣ ገዥ ትርክትን በማስረጽ፣ በትጋት እና በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት!
Next articleላሊበላ ወደ ቀደመ ማንነቷ እንድትመለስ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።